ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሚኖሩባት የቨርጂኒያ ምርጫ የሪፐብሊካን ዕጩ እየመሩ ነው
በርካታ ትቅልደ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባት የአሜሪካዋ ቨርጂኒያ ግዛት እየተካሄደ ባለው የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ምርጫ የሪፐብሊካኑ ዕጩ ግሌን ዮንከን ተቀናቃኛቸውን እየመሩ መሆኑ ተነገረ።
አንዳንድ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ከአሁኑ ግሌን ዮንከን ማሸነፋቸውን ይፋ ማድረግ ጀምረዋል።
ከጥቂት ሰዓታት በፊት በነበረ ውጤት ግሌን ዮንከን በ2.7 ነጥብ የዲሞክራቱን ዕጩ ቴሪ መካሌፍ ቀድመዋቸዋል።
እስከ አሁን 95 ከመቶ የሚሆው ድምጽ ተቆጥሯል።
የዲሞክራቱ ዕጩ ሚስተር መካሌፍ በፈረንጆች 2014 እስከ 2018 ድረስ ለአራት ዓመታት የግዛቷ ገዢ ሆነው ያገለገሉ ናቸው።
ይህ ምርጫ ጆ ባይደን ፕሬዝዳንትነት ከተመረጡ በኋላ ዲሞክራቶች በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት መለኪያ ተደርጎ ተወስዷል።
በዚህ ግዛት ዲሞክራቶች ከተሸነፉ የጆ ባይደን ቅቡልነት ማጣት አንድ ማሳያ እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ጆ ባይደን ቨርጂኒያን በ10 ነጥብ የበላይነት ማሸነፋቸው አይዘነጋም።
አሁን የገዥነት ምርጫውን እየመሩ የሚገኙት ግሌን ዮንከን ባደረጉት የድል ንግግር "ይህ ወሳኝ ድል ነው" ብለዋል።
የዲሞክራቱ ዕጩ ቴሪ በበኩላቸው ሽንፈቱን ገና ያልተቀበሉ ሲሆን ለደጋፊዎቻቸው "ጊዜው ገና ነው" እያሉ ነው።
ከቨርጂኒያ ሌላ በኒው ጀርሲም በዲሞክቶችና በሪፐብሊካን መካከል ጥብቅ ፉክክር እየተደረገ ነው።
ጆ ባይደን ወደ ዋይት ሐውስ ከገቡ ወዲህ የዋጋ ግሽበት መባባስ፣ የተቀዛቀዘው የምጣኔ ሀብት ቶሎ አለማንሰራራት እና ዝርክርክ የተባለው የአሜሪካ ከአፍጋኒስታን የወጣችበት መንገድ በሕዝብ ዘንድ ለዲሞክራቶች የነበረው ተስፋና እምነትን ሸርሽሯል እየተባለ ነው።
በርካታ ትውልድ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን በሚገኙባት ቨርጂኒያ አሸናፊው ማን እንደሆነ በይፋ ማምሻውን ይለይለታል ቢባልም ፎክስ ኒውስን ጨምሮ በርካታ የአሜሪካ ሚዲያዎች አሸናፈው የሪፐብሊካኑ ግሌን ዮንከን መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል።