ከሁለት ሳምንታት በላይ ጠፍታ የነበረችው የአራት አመት ህጻን ተገኘች

በአውስትራሊያ ገጠራማ አካባቢ ለ18 ቀናት ጠፍታ የነበረው አንዲት የአራት አመት ህጻን በአንድ ቤት ውስጥ ተቆልፎባት መገኘቷን ፖሊስ አስታወቀ።

ክሊኦ ስሚዝ የተሰኘችው ይህች ህጻን ከቤተሰቧቿ አይን የተሰወረችው በካርናርቮል ከተማ ነበር። ይህንን ተከትሎ ነው ፖሊስ ባካሄደው ከፍተኛ ፍለጋ በአንድ ጎልማሳ ቤት ውስጥ ልትገኝ የቻለችው።

ፖሊስ የ 36 አመቱን ግለሰብ መኖሪያ ቤት ሰብሮ በመግባት ህጻኗን ያዳነ ሲሆን ግለሰቡንም በቁጥጥር ስር አውሎ በመመርመር ላይ ይገኛል። የምዕራብ አውስትራሊያ የፖሊስ ምክትል ኮሚሸነር ኮሎኔል ብላንች ናቸው ይህንን ያስታወቁት።

ህጻኗ በተገኘች ወቅት የቀረበላት የመጀመሪያው ጥያቄ ስምሽ ማነው የሚል ሲሆን ለአንደኛው የፖሊስ አባልም ስሟን መናገሯን ኮሎኔሉ አክለዋል።

ህጻኗ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከቆዩት ከቤተሰቦቿ ጋር የተገናኘች ሲሆን 'ቤተሰባችን አሁን ተሟልቷል' ሲሉ የህጻኗ እናት ኢሊ ስሚዝ በኢንስታግራም ገጻቸው ላይ ገልጸዋል።

ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ ከህጻኗ ቤተሰብ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ገልጿል። እንዲሁም ፖሊስ ክሊኦ ያስመለጠበትን ሁኔታ አስመልክቶ የሚለው ነገር እንዳለው እና ይህንንም ግዜው ሲደርስ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቐል።

ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ጉባኤ ከተጓዙበት ስኮትላንድ ወደ አገራቸው እየተመለሱ ያሉት የአውስትራሊያው ፕሬዘዳንት በታዳጊዋ መገኘት ዜና መደሰታቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።

ባለስልጣናት ሕጻኗ የት እንዳለች ለሚጠቁም ሰው አንድ ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጡ ቃል ገብተው ነበር።

የክሊኦ ቤተሰቦች ለመዝናናት በሄዱባት ከተማ በተጣለው ድንኳን ውስጥ ክሌኦ እና እህቷ በድንኳኑ አንደኛ ክፍል ተኝተው የነበረ ሲሆን እናቷ በቀጣዩ ቀን ጠዋት ወደ ልጆቿ ክፍል ስትሄድ ክሊኦን እንዳጣቻት ተናግራለች።

ይህንን ተከትሎም ፖሊስ በመሬት፤ በአየር እንዲሁም በባሕር ላይ ባሰማራው ቡድን ታዳጊዋን ሲያፈላልግ ቆይቶ በመጨረሻም ሊያገኛት ችሏል። የህጻኗ መጥፋት ከአገር ውስጥ አልፎ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቦ ነበር።