በኡጋንዳ 5 የኤርትራ ከ20 ዓመት በታች ሴት ብሔራዊ ቡድን አባላት ጠፉ

በኡጋንዳ እየተካሄደ በሚገኘው ቀጣናዊ የእግር ኳስ ውድድር ተሳታፊ የነበረው የኤርትራ ከ20 አመት በታች የሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን አምስት አባላት መጠፋታቸው ተዘግቧል።

አምስቱ ተጫዋቾች ትላንት [ማክሰኞ] ጠዋት ካረፉበት ሆቴል የተሰወሩ ሲሆን በሴካፋ ከ20 አመት በታች የሴቶች ሻምፒዮና የኤርትራ ብሄራዊ ቡድን አባል ነበሩ።

ባለፈው ቅዳሜ የጀመረው እና እስከ ህዳር 9 የሚከናወነ ውድድር ኒጄሩ በተባለ የኡጋናዳ ከተማ ውስጥ የሚካሄድ ነው።

በሁለት ዓመት ውስጥ በሴካፋ ከ20 አመት በታች ሻምፒዮና የኤርትራ ቡድን አባላት ሲጠፉ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 በኡጋንዳ አምስት ኤርትራዊያን ወንድ ተጨዋቾች ሆቴላቸውን ጥለው ሸሽተው ነበር።

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት ሴካፋ] ባወጣው መግለጫ ጉዳዩ ለፖሊስ ሪፖርት እንደተደረገና ምርመራም በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጻል።

ከኡጋንዳ ከተገኘ መረጃ በተቃራኒ የሴካፋ ዋና ዳይሬክተር አውካ ጌቾ ተጨዋቾች እንዳይሸሹ በቂ እርምጃዎች ተወስደዋል ሲሉ ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ተናግረዋል።

ሴካፋ ከዩጋንዳ የእግር ኳስ ባለስልጣን ጋር የጠፉ ተጫዋቾችን ለማግኘት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

“ጉዳዩን ለባለሥልጣናት ሪፖርት አድርገን አስፈላጊውን መረጃ ሁሉ ሰጥተናል ከኡጋንዳ እግር ኳስ ባለሥልጣናት [ፉፋ]ጋር ተባብረን እንሰራለን’’ ያሉ ሲሆን "በቦታው በቂ የደህንነት ጥበቃ እንደነበር እንዲሁም ሁሉም ቡድኖች በጥሩ ሁኔታ ሆቴሎች ውስጥ መሆናቸውን ፉፋ አረጋግጣልን ነበር” ሲሉ አክለዋል።

"ተመሳሳይ ሁኔታ ከዚህ በፊት ተከስቷል፣ ባለሥልጣናቱ ከዚህ ቀደም የሆኑ ነገሮችን ጠንቅቀው ያውቃሉ። በክልላችን ሁሉን አቀፍ ውድድሮችን ለማድረግ የተጣለብንን ተልእኮ በማረጋገጥ ከባለሥልጣናት ጋር በቅርበት መስራታችንን እንቀጥላለን" ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በ2019 በኡጋንዳ ከጠፉት ከ20 ዓመት በታች የኤርትራ ብድን አባላት በተጨማሪ እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 10 ኤርትራዊያን ተጫዋቾች ከቦትስዋና የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ወደ ሀገራችን አንመለስም ያልሆኑ ሲሆን በኡጋንዳ ደግሞ በ2013 15 ተጫዋቾች እና የቡድኑ ሃኪም ጥገኝነት ጠይቀው ይሁንታን አግኝተዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2009 ደግሞ ከአሰልጣኙ እና ከቡድኑ አመራር በስተቀር በኬንያ የሴካፋ ውድድር ተሳታፊ የነበረው የኤርትራ ሙሉ ቡድን ወደ ሀገረሩ ሳይመለስ ቀርቷል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኤርትራ አለ በሚባለው የሰብአዊ መበት ጥሰት በሺህ የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ሀገራቸውን ጥለው እየተሰደዱ ነው ሲል ገልጻል።

ሆኖም የኤርትራ መንግሥት እነዚህን ውንጀላዎች ውድቅ ያደርጋቸዋል። የሸሹት ሰዎች ቁጥርም የፈጠራኣ ወሬ ናቸው ሲልም ተደምጧል።