ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዐቃቤ ሕግ ህወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ቢያንስ 482 ግድያዎችን ፈጽሟል አለ
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህወሓት አማጺያን በተቆጣጠሯቸው የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች ከ482 በላይ ንጹሃን ሰዎችን ገድለዋል ሲል ከሰሰ።
ይህ የተገለጸው በፍትሕ ሚኒስቴር የዐቃቤ ሕግ ዘርፍ እና የፌደራል ፖሊስ የምርመራ ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች ያካሄዱት የመጀመሪያ ደረጃ የወንጀል ምርመራ ውጤት ይፋ በተደረገበት ወቅት ነው።
የምርመራ ቡድኑ ከግድያው በተጨማሪ በሁለቱ ክልሎች 165 የአካል ጉዳቶች እንዲሁም 109 የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች በህወሓት ኃይሎች ተፈጸመዋል ብሏል።
በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው እና ወደ አጎራባች ክልሎች የተስፋፋው ጦርነት አንድ ዓመት ሊሆነው የተቃረበ ሲሆን፤ ቁጥራቸው በትክክል የማይታወቁ ሰዎችን ለሞት ዳርጓል።
በተጨማሪም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንበረታቸው ሲፈናቀሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል።
በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑት አካላት በሙሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል በሚል በተደጋጋሚ ክስ ሲቀርብባቸው ቆይቷል።
በጦርነቱ ውስጥ ተፈጽመዋል የባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጋር በመሆን እያደረጉ ያሉት ምርመራ ውጤት በቅርቡ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የዐቃቤ ሕጋና የፖሊስ ምርመራ
ምርመራው የተካሄደው በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ በፌደራል ፖሊስ እንዲሁም ከክልል አካላት ጋር በትብብር በተዋቀረ የዐቃቤ ሕግ እና የፖሊስ የምርመራ ቡድን ነው።
መርማሪ ቡድኑ እነዚህ ወንጀሎች የተፈጸሙት የፌደራሉ መንግሥት ሰኔ 2013 ላይ የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ አካባቢዎች መውጣቱን ተከትሎ የህወሓት አማጺያን ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ከገቡ በኋላ ነው ብሏል።
ምርመራው ትኩረት ያደረገው በአማራ ክልል በደቡብ እና በሰሜን ጎንደር ዞን አካባቢዎች ሲሆን በአፋር ክልል ደግሞ ጋሊኮማ ቀበሌን ጨምሮ በፈንቲረሱ ዞን ስር በሚገኙ አካባቢዎች ነው።
የምርመራ ቡድኑ የወንጀል ድርጊቶቹ የተፈጸሙት ከሐምሌ 2013 ዓ.ም ጀምሮ አካባቢዎቹ በፌዴራል እና በክልል የጸጥታ አካላት ቁጥጥር ስር ተመልሰው እስከ ገቡበት ጊዜ ድረስ ባሉት ጊዜያት መሆኑን አመልክቷል።
ምርመራው እንዴት ተካሄደ?
በደቡብ ጎንደር ዞን የተሰማራው የምርመራ ቡድን ከ790 በላይ ምስክሮችን የምስክርነት ቃል፣ በሰሜን ጎንደር ዞን የተሰማራው የምርመራ ቡድን ደግሞ 285 የምስክሮች ቃል እንዲሁም በአፋር ክልል የተሰማራው ቡድን 148 ምስክሮች ቃል መቀበሉን አመልክቷል።
ከምስክርነት ቃል በተጨማሪ ተፈጽመዋል የተባሉት የወንጀል ድርጊቶችን ሊያስረዱ የሚችሉ የሰነድ ማስረጃዎች አሰባስቢያለሁ ብሏል።
የወንጀል ምርመራ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት
ምርመራው የህወሓት አማጺያን በሰሜን ጎንደር ዞን የ96 ሰዎች ሞት፣ 53 የአካል ጉዳት፣ 29 አስገድዶ መደፈር፣ 11 ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ እና እገታን ጨምሮ በንብረት ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋና ውደመት አድርሷል ብሏል።
በደቡብ ጎንደር ዞን ባሉ አምስት ወረዳዎች ደግሞ የ129 ሰዎች ሞት፣ የ54 ሰዎች የአካል ጉዳት፣ ከ73 በላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንዲሁም በርካታ ግለሰቦች ንብረት ላይ ውድመት ደርሷል።
በአፋር ክልል ደግሞ የ257 ሰዎች ሞት፣ የ59 ሰዎች የአካል ጉዳት እና በ7 ሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች እንደተፈጸመባቸው ተረጋግጧል ብሏል መርማሪ ቡድኑ በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ።
የዐቃቤ ሕግ እና የፖሊስ የምርመራ ቡድን የህወሓት አማጺያን ይህን መጠነ ሰፊ ጥቃት የፈጸሙበት ዋንኛ ዓላማ በብሔር የተመሰረተ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ያለመ ነው ብሏል።
ይህ በተፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ የተደረገ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ሲሆን ቀጣይ ምርመራ እንደሚኖር ተገልጿል።