የዱባዩ መሪ የቀድሞ ባለቤታቸውን ስልክ እንዳስጠለፉ ፍርድ ቤት ገለጸ

ልዕልት ሃያና ሼክ መሃመድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዱባዩ መሪ ሼክ ሞሐመድ አል ማክቱም የቀድሞ ባለቤታቸው የጆርዳን ልዕልት ሀያን ስልክ እንዳስጠለፉ የዩናይትድ ኪንግደም ፍርድ ቤት ገለጸ።

ፍቺ እያካሄዱ ባለበት ወቅት የልዕልቷ ወገን የሆኑ ሌሎች ሰዎችም ስልክ እንዲጠለፍ አድርገዋል።

ልዕልቷ ይህንን ዜና ከሰማች በኋላ "እየታደንኩ እንዳለሁ ነው የሚሰማኝ" ብላለች።

የዱባዩ መሪ የልዕልቷ ስልክ ስለመጠለፉ መረጃው የለኝም ብለው ምላሽ ሰጥተዋል።

ፍርድ ቤቱ ስለ ስልኩ መጠለፍ መረጃ ይፋ ያደረገው እሳቸውን ባላሳተፈ ምርመራ መሆኑን ገልጸው "ፍትሐዊ አካሄድ አይደለም" ሲሉ አክለዋል።

የፍርድ ቤቱ ግኝት የዱባዩ መሪ የጆርዳኗን ልዕልዕት ጨምሮ ሌሎችም ሴት የቤተሰብ አባሎቻቸው ላይ የሚያደርሱት በደል አንድ ማሳያ ነው ተብሏል።

ፍርድ ቤቱ እንዳለው፤ የሰዎችን ስልክ ማስጠለፍ በዩኬ የወንጀለኛ መቅጫ እንዲሁም በሌሎችም ድንጋጌዎች ያስቀጣል።

ከልዕልቷ ባሻገር ከሷ ጋር በቅርበት የሚሠሩ ተቀጣሪዎቿ ስልክም ተጠልፏል። ሁለት የደኅንነት ክፍል ሠራተኞቿን ስልክ ለመጥለፍም ሙከራ ተደርጓል።

የልዕልቷን ስልክ ለመጥለፍ ጥቅም ላይ የዋለው ፔገሰስ የተባለው መተግበሪያ ነው።

በእስራኤሉ ኤንኤስኦ ግሩፕ የተመረተው ፔገሰስ መተግበሪያ ከዘህ ቀደም ጋዜጠኞችን ጨምሮ በርካታ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን ስልክ ለመጥለፍ መዋሉ አይዘነጋም።

ፔገሰስ የስልኩ ባለቤት ያለበት ቦታ መለየት፣ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ማንበብ፣ የስልክ ጥሪ ማዳመጥ፣ ኢሜል ማንበብ፣ ፎቶ ማየት፣ ሌሎች መተግበሪያዎችን ሰብሮ መግባት፣ የይለፍ ቃል መመዝገብ እና የቀን መቁጠሪያ ላይ የተመዘገቡ አጀንዳዎችን ማግኘት ይችላል።

የስልኩ ባለቤት ሳያውቅ ድምጽና ምስል መቅረጽ የሚችልም አደገኛ የስለላ መተግበሪያ ነው።

ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን በተለያዩ አገራት የሚኖሩ የቤተሰብ አባሎቻቸው ላይ ለመሰለል ተመሳሳይ መተግበሪያ ተጠቅመዋል ተብሎ ነበር።

የሳዑዲው ጋዜጠኛ ጀማል ካሾግጂ አጋሮች በዚህ ስለላ መረብ ውስጥ ወድቀው ከነበሩ መካከል ይጠቀሳሉ።

በልዕልት ሀያ እና በመሪው ሼክ ሞሐመድ መካከል እየተካሄደ ባለው የፍርድ ቤት ክርክር ልዕልት ሀያን የሚወክሉ የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ሼክ ሞሐመድ የልዕልት ሀያ ስልክ እንዲጠለፍ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ከልዕልት ሀያ ስልክ 265 ሜጋባይት መረጃ መሰረቁን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።

ሼክ ሞሐመድ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ቢሉም ዶ/ር ዊልያም ማክዛክ የተባለ የቴክኖሎጂ ባለሙያ የልዕልቷ ስልክ መጠለፉን ለፍርድ ቤቱ ምስክርነት ሰጥቷል።

ስልኩ የተጠለፈው ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሊሆን እንደሚችልም ባለሙያው አስረድቷል።

የቀድሞው የዩኬ ጠቅላይ ሚንስትር ባለቤት ቼሪ ብሌር፤ ለልዕልት ሀያ ስልክ በደወሉላት ወቅት ነበር የልዕልቷ ስልክ እንደተጠለፈ የታወቀው።

ለቼሪ ብሌር ከእስራኤል ስልክ ተደውሎ በፔገሰስ መተግበሪያ ስልካቸው በስህተት መጠለፉ ተነገራቸው። ከዚያም የተጠለፈው የልዕልት ሀያ ስልክ እንደሆነ ተደረሰበት።

ልዕልት ሀያ የልጇቿ ሕጋዊ ጠባቂ ለመሆን በፍርድ ቤት እየተከራከች ነው። ከሳዑዲው መሪ የተለያየ ጫና እደረሰባትም ይገኛል።

"ለሕይወቷ እየሰጋች ነው የምትኖረው። የልጆቿ ደኅንነትም ያስፈራታል" ሲሉ ጠበቆቿ ተናግረዋል።

የዱባዩ መሪ ከዚህ ቀደም ልዕልት ሀያ ዩኬ የምትኖርበት ቤት አቅራቢያ ቤት ገዝተው ለመሰለል ሞክረዋል።

ልዕልቷ "እያሳደዱኝ ነው። ከልጆቼ አባት የት እንደምደበቅ አላውቅም። በጣም ጨቋኝ ነው" ስትል ለፍርድ ቤት ተናግራለች።

ሼክ ሞሐመድ ሸኪያ ላቲፋ እና ሸኪያ ሻምሳ የተባሉ ልጆቻቸውን በግዳጅ ወደ ዱባይ መውሰዳቸውን ፍርድ ቤት አረጋግጧል።

ሸኪያ ላቲፋ በአባቷ እስረኛ እንደሆነች ስትናገር የሚያሳይ ሚስጥራዊ ቪድዮ ቢቢሲ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።