አሜሪካዊው የቀድሞ ሴት ጓደኛውን እርግማን ለማስወገድ ቃል የገባችውን 'አዋቂ' ከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በካሊፎርኒያ አንድ ግለሰብ በቀድሞ የሴት ጓደኛው በተቀጠረች ጠንቋይ አማካኝነት በትዳሩ ላይ የተጣለውን እርግማን አስወግዳለሁ ብላ ቃል የገባችን 'አዋቂ' ከሷል።
ግለሰቡ ይህች አዋቂ በሃሰት ገንዘብ አጭበርብራኛለችም ሲል ነው ክሱን ያቀረበው።
ማውሮ ሬስትሬፖ የተባለው ግለሰብ ባቀረበው ክስ መሰረት አዋቂ የተባለችው ሶፊያ አዳምስ እርግማኑን ለማስወገድና ትዳሩን ለማዳን 5 ሺህ 100 ዶላር እንዳስከፈለችው ነው።
የማጭበርበር ክሱም በቶራን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቧል።
እርግማኑ ካልተነሳ እሱም ሆነ ቤተሰቡ "ደስተኛ እንደማይሆኑና አደጋ ላይ እንደሚወድቁ" አዋቂዋ ነግራኛለች ሲልም ማውሮ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
በዚህም ጉዳት ደርሶብኛል የሚለው ግለሰቡ 25 ሺህ ዶላር ካሳም ይከፈለኝ ብሏል።
ከማጭበርበር በተጨማሪ ሌሎች ተጨማሪ ክሶችም ያቀረበ ሲሆን ከነዚህም መካከል የቸልተኝነት፣ ማሴር እና ሆን ተብሎ የስሜት መጉዳት ይገኙበታል።
የማውሮና የአዋቂዋ ግንኙነት የሚጀምረው ግለሰቡ በኢንተርኔት ጉግል ላይ በፍለጋ ካገኛት በኋላ ነው።
የሶፊያ ድረ ገፅ "የፍቅር ስፔሻሊስትና"፣ "የህይወት አሰልጣኝ ዶክተር" በሚልም ነው የሚገልጻት።
በድረገፁም ላይ የተሰጠው መረጃ "ከሳሹን ሊረዳው ከሚችል ባለሙያ ጋር እየተነጋገረ ስለመሆኑ የበለጠ መተማመን እንዲሰጠው አድርጎታል" ይላል ክሱ።
ግለሰቦቹ በነበራቸው ቆይታ ሶፊያ ካርዶችን አንብባ በቀድሞ የሴት ጓደኛው በተቀጠረ ጠንቋይ አማካኝነት "ማላ ሱርቴ" ወይም መጥፎ እድል አንደመጣበት ነግራዋለች።
እርግማኑ እስካልተወገደ ድረስ የማውሮን፣ የልጆቹንም ህይወትና ትዳሩን እንደሚያበላሸው መናገሯን ለፍርድ ቤት የቀረበው ክስ ያስረዳል።












