ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ ከእስር እንዲለቀቅ ተጠየቀ

ተስፋዓለም

የፎቶው ባለመብት, Photo by Melody Sundberg

የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረገጽ መስራችና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ በአስቸኳይ እንዲፈታ ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገቱት ኮሚቲ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (ሲፒጄ)ና ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደስ ጠየቁ።

ተስፋዓለም በኢትዮጵያ ኢንሳይደር የማኅበራዊ ትስስር ገፁ በኢሬቻ በዓል ላይመስከረም 25፣ 2014 ዓ.ም የተነሳውን ተቃውሞ ቪዲዮዎች ከለጠፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በቁጥጥር ስር መዋሉን ሲፒጄ ገልጿል።

የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ በፌደራል ፖሊስ እጅ ስር እንደሚገኝ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ኃላፊው እንደተናገሩት ተስፋዓለም በአሁኑ ጊዜ "የፌደራል ፖሊስ የምርመራ ቢሮ የሜክሲኮ ማቆያ እንደሚገኝ" ገልጸው፤ "ምንም የሚፈጠር ነገር የለም። ያለውን ነገር እያጣራን ነው። ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የወንጀል ምርመራ ቢሮ ምክትል ኃላፊው፤ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም በቁጥጥር ሥር ስለዋለበት ጉዳይ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ይህ ተግባር "መንግሥት በፕሬሱ ላይ ነፃ የሆነ ወይንም የተቃውሞ ሽፋንን ከማበረታት ይልቅ ለማፈን የሚያደርገው ተከተታይ ጥቃቶችን የሚያጋልጥ ነው" በማለት ሲፒጄ በትዊተር ገጹ አስፍሯል።

ሲፒጄ ፖሊስ ጋዜጠኛውን በአስቸኳይ እንዲፈታውም ጠይቋል።

ተስፋዓለም ከዚህ ቀደም በሽብር ወንጀል ከአንድ ዓመት በላይ መታሰሩን ድርጅቱ ጠቁሞ "የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደቀደመው ሚዲያው አፈና ስልቶች መመለሱ የሚያሳዝን ነው" ብሏል።

ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ በበኩሉ በትዊተር ገጹ በበዓሉ ላይ የተሰማውን ተቃውሞ ሲቀርጽ በቁጥጥር ስር የዋለው ተስፋዓለም በአስቸኳይ እንዲፈታ ኢትዮጵያ ባለስልጣናትን ጠይቋል።

"በአገሪቱ ውሰጥ የፀረ መንግሥት ተቃዋሚዎችን መቅረጽ ክልክል ነው? ከሥራው በስቀር ምንም አላደረገም። ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም" ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።

ተስፋዓለም ወደልደየስ ዜናና ትንታኔ የሚቀርብበት 'ኢትዮጵያ ኢንሳይደር' የተባለው ድረገጽ መስራችና ዋና አዘጋጅ ሲሆን፤ ገጹ በተለይ ወቅታዊ የፖለቲካ ዜናዎችን በማቅረብ እየታወቀ ያለ ከመሆኑ በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይም በርካታ ተከታዮችን በማፍራት ላይ ያለ ነው።

ቢቢሲ ከታማኝ ምንጮቹ መረዳት እንደቻለው ጋዜጠኛ ተስፋዓለም በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ መኖሪያ ቤቱ ላይ ፍተሻ መካሄዱን ገልጸዋል።