ለሰዓታት ተቋርጠው የነበሩት ፌስቡክ፣ ዋትስአፕና ኢንስታግራም ተመለሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎቶቹ ፌስቡክ፣ ዋትስአፕ እና ኢንስታግራም ለስድስት ሰዓታት ያህል ተቋርጠው ከቆዩ በኋላ መመለሳቸውን ፌስቡክ አስታውቋል።
ኩባንያው ለአገልግሎቶቹ መቋረጥ የሰጠው ምክንያት የተሳሳተ የአወቃቀር ለውጥ ጋር የተያያዘ ነው ይላል።
በፌስቡክ ባለቤትነት ስር ያሉት እነዚህን የማህበራዊ ሚዲያዎች በደስክቶፕ፣ በላፕቶፕም ሆነ በተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ መስራት አቁመው ነበር።
የአገልግሎት መቆራረጥን የሚከታተለው ዳውንዲቴክተር የተባለው ድርጅት 10.6 ሚሊዮን ሰዎች ሪፖርት እንዳደረጉ ጠቅሶ በዓለማችን ከተከሰቱ ትልቁ ውድቀት ነው ሲልም ጠርቶታል።
አገልግሎቶቹ የተቋረጡት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ወደ 1 ሰዓት ገደማ ሲሆን የተመለሱትም ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ነው።
ፌስቡክ በዛሬው ዕለት ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ የተሳሳተ የአወቃቀር ለውጥ መከሰቱን ተከትሎ በአጠቃላይ የኩባንያውን ውስጣዊ መሳሪያዎች እና ስርዓቶች ላይ ተፅእኖ በማሳደሩ ችግሩን ለመፍታት አዳጋች አድርጎታል ብሏል።
መግለጫው አክሎም "ተቋርጠው በነበሩበት ሰዓታት የተጠቃሚዎች ግላዊ መረጃ ተጥሷል የሚል ማስረጃ የለም" ብሏል።
የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙከርበርግ አገልግሎቶቹ በመቋረጣቸው ምክንያት ለተጎዱ ሰዎች ይቅርታ ጠይቀዋል።
በዚህ ደረጃ አገልግሎቶቹ መቋረጥ የተለመደ ክስተት አይደለም። ከሁለት ዓመታት በፊት ፌስቡክ እና ሌሎች መተግበሪያዎቹ በመቋረጣቸው በዓለም ዙሪያ ከ14 ሰዓታት በላይ ተደራሽ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።
ሬዲትና እና ትዊተርን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በአገልግሎቶቹ መቋረጥ ሲሳለቁ አምሽተዋል።
መቋረጡ የተከሰተው ስለ ኩባንያው ሰነዶችን ይፋ ያደረጉ የቀድሞ የፌስቡክ ሠራተኛ ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስ ማግስት ነው።
ፍራንቼስ ሀውገን የተባሉት ግለሰብ እሁድ እለት ለሲቢኤስ ዜና እንደተናገሩት ኩባንያው "ከደህንነት በፊት ቅድሚያ ለእድገት ሰጥቷል" ብለዋል።












