አንድ የአስራኤል አየር ኃይል መኮንን ለማግኘት ሞሳድ ያደረገው ጥረት እያነጋገረ ነው

ሌፍትናንት ኮሎኔል ሮን አራድ

የፎቶው ባለመብት, Prime Minister of Israel

የምስሉ መግለጫ, ሌፍትናንት ኮሎኔል ሮን አራድ

የእስራኤል የሰላላ ተቋም ሞሳድ ከዓመታት በፊት የጠፋውን የእሰራኤል የአውሮፕላን አቅጣጫ ጠቋሚ (ናቪጌተር) ለማግኘት "ድፍረት የተሞላበት" ፍለጋ ማካሄዱን የእስራኤል ጠቅላይ ሚንሰትር ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚንስትር ናፍታሊ ቤኔት ለእስራኤል ፓርላማ ሮን አራድ የተባለው የአየር ኃይል መኮንን መጨረሻ ምን እንደሆነ ለማወቅ ሞሳድ ፍላጋ ማካሄዱን ከመናገር ውጪ ስለ ኦፕሬሽኑ ዝርዝር መረጃ መስጠት አልችልም ብለዋል።

በእስራኤላውያን ዘንድ ምስጢር ሆኖ የቀረውን የሌፍትናንት ኮሎኔል ሮን አራድ ጉዳይ ለማወቅ የተደረገው ኦፕሬሽን ስኬታማነት በመለከተ እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ መረጃዎችን እየወጡ ይገኛሉ።

ሌፍትናንት ኮሎኔል ሮን አራድ እአአ 1986 ላይ ይጓዝበት የነበረው የጦር አውሮፕላን ሊባኖስ ውስጥ ከተከሰከሰ በኋላ ሕይወቱ አልፏል ተብሎ ተደምድሞ ነበር።

በወቅቱ አውሮፕላኑን አብራሪ በእስራኤል ወታደሮች ነጻ ወጥቶ ነበር። የአውሮፕላኑ አቅጣጫ ተቋሚ የነበረው ሌፍትናንት ኮሎኔል ሮን አራድ ግን አማል በተባለው የሊባኖስ የሺዓ ሙስሊም ሚሊሻ ቡድን ተይዞ ነበር።

ከአንድ ዓመት በኋላ አማል የተሰኘው የሚሊሻ ቡድን ሌፍትናንት ኮሎኔል ሮን አራድን በ200 የሊባኖስ፣ 450 ፍልስጤማውያን እስረኞች እና በ3 ሚሊዮን ዶላር ለመለዋወጥ ለእስራኤል ጥያቄ አቀርቦ ነበር።

ይሁን እንጂ እስራኤል ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለመልቀቅ ፍቃደኛ ስላልነበረች ስምምነቱ ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል።

ሌፍትናንት ኮሎኔል ሮን አራድ መጨረሻም በእስራኤላውያን ዘንድ ግልጽ ሳይሆን ቀረ።

እአአ 2016 ላይ ደግሞ ሞሳድ እና የእስራኤል ጦር ደኅንነት ሌፍትናንት ኮሎኔል ሮን አራድ በቁጥጥር ሥር ከዋላ ከሁለት ዓመታት በኋላ ማለትም እአአ 1988 ላይ በእሰር ላይ እያለ ሕይወቱ አልፏ ሲሉ ከድምዳሜ ደርሰው ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር ቤኔት፤ ከአንድ ወር በፊት ወንድ እና ሴት የሞሳድ አባላት የሌፍትናንት ኮሎኔል ሮን አራድ መጨረሻ እና መገኛን በተመለከተ መረጃ ለመሰብሰብ "ውስብሰብ፣ ሰፊ እና ጠንካራ ኦፕሬሽን" ለማካሄድ ተንቀሳቅሰዋል ሲሉ ለፓርላማው ተናግረዋል።

"በአሁኑ ወቅት ላጋራ የምችለው ይህን መረጃ ብቻ ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ ለአገሪቱ ፓርላማ።

ቻናል 12 የተባለ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ በሞሳድ የተካሄደው ኦፕሬሽን አልተሳክም ሲል ዘግቧል።

ቻናል 12 የሞሳድ አለቃ በአንድ ሰብሰባ ላይ፤ "ድፍረት የተሞላበት፣ ውስብስብ ኦፕሬሽን ነበር፤ ግን አልተሳካም" ሲሉ ተናግረዋል ሲል ዘግቧል።

የቻናል 12 ዘገባን ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ኦፕሬሸኑ አልተሳካም መባሉ ሐሰት ነው ብሎ፤ ተልዕኮው የተሳካ ነበር ብሏል።

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ መስጠት የኦፕሬሽኑ ተልዕኮ ላይ አሉታዊ ውጤት ሰለሚያስከትል ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት መቆጠቡን ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት የወጣው መግለጫ አትቷል።

የሌፍትናንት ኮሎኔል አራድ ቤተሰቦች በበኩላቸው፤ "አንድ ቀን የሮን መጨረሻ ምን እንደሆነ እናውቃለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ይላሉ።