ፌስቡክ፣ ዋትስአፕ እና ኢንስታግራም ያጋጠማቸው ምን ነበር?

ፌስቡክ ዋትስአፕ ኢንስታግራም

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፌስቡክ ኩባንያ በመላው ዓለም አገልግሎቱ ለበርካታ ሰዓታት ተቋርጦ ከቆየ በኋላ ተጠቃሚዎቹን ይቅርታ ጠይቋል።

በፌስቡክ ባለቤትነት የሚተዳደሩት ዋትስአፕ እና ኢንስታግራምም ከፌስቡክ ጋር በተመሳሳይ ለሰዓታት ተቋርጠው ቆይተው ነበር።

ያጋጠመው ችግር ምን ነበር?

የፌስቡክ ሥርዓቶች ሙሉ ለሙሉ መሥራት አቁመው ነበር። ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ በመተግበሪያዎችም ሆነ በድረ-ገጻቸው አማካኝነት አገልግሎታቸውን ማግኘት ሳይቻል ቆይቶ ነበር።

የድረ-ገጾች ግንባታ ተቋም የሆነው ክላውድፍሌር ፌስቡክ ኩባንያ ያጋጠመውን ችግር፤ "አንድ ሰው የዳታ ገመዳቸውን በአንድ ጊዜ ነቅሎ የኢትንተርኔት ግንኙነታቸውን ያቋረጠ ይመስላል" በማለት ያጋጠመውን ችግር በቀላል ቋንቋ ለመግለጽ ሞክሯል።

ፌስቡክ በበኩሉ ላጋጠመው ችግር የሰጠው ማብራሪያ ግን ወሰብሰብ ያለ ነው።

በዳታ ማዕከሎቻችን ላይ የኔትዎርክ ትራፊክ የሚያቀላጥፉ ራውተሮች ላይ የተካሄደው የመዋቅር ለውጥ ግንኙነት እንዲቋረጥ ምክንያት ሆኗል ብሏል።

ኢንተርኔት በመቶ ሺዎች በሚቆጠር ኔትዎርኮች ይከፋፈላል። እንደ ፌስቡክ ያሉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የራሳቸው የሆነ ግዙፍ ኔትዎርኮች አሏቸው።

ለምሳሌ አንድ ሰው በላፕቶፕ ኮምፒዩተሩ ፌስቡክ መጠቀም ቢፈልግ፤ ኮምፒዩተሩ በብሮደር ጌትዌይ ፕሮቶኮል አማካኝነት ከፌስቡክ ኔትዎርክ ጋር መገናኘት አለበት።

ሰዎች መጎብኘት ወደ ፈለጉት ድረ-ገጾች እንዲያመሩ ብሮደር ጌትዌይ ፕሮቶኮል ዳታ ሊንቀሳቀስ የሚችልበትን እና የተሻለውን አማራጭ ይለያል።

ችግሩ ያጋጠመውም ፌስቡክ በድንገት ይህንን ሥርዓት በአግባቡ ለማከናወን የሚፈልገውን መረጃ መስጠት በማቆሙ ነው። ይህም የፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ አገልግሎቶች እንዳይኖሩ አድርጓል።

የችግሩ መነሻ በሰዎች ስህተት ይሁን በሶፍትዌር ብልሽት እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። ይሁን እንጂ ለአገልገሎቶቹ መቋረጥ በርካታ ያልተረጋገጡ መላምቶች እየተሰጡ ነው።

ከእነዚህም መካከል፤ ውስጥ አዋቂ የፌስቡክ ሠራተኛ ሆነ ብሎ ግንኙነቶችን አቋርጧል የሚል ይገኝበታል።

ይህ እንዴት ሊከሰት ቻለ?

አገልግሎቶቹ የተቋረጡት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ምሽት 1 ሰዓት ገደማ አካባቢ ነበር። ፌስቡክ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ ከስድስት ሰዓታት በላይ ወስዶበታል።

የኒው ዮርክ ታይምስ ዘጋቢው ሺር ፍሬንኬል ችግሩ ሳይቀረፍ ረዥም ሰዓታትን የወሰደበትን ምክንያት ለቢቢሲ ሲያስረዳ፤ "ችግሩ ምን እንደሆነ የሚያጣሩት ሰዎች በአካል ወደ ሕንጻው መግባት እንኳ አልቻሉም ነበር" በማለት ተናግሯል።

ከፍተኛ ተጠቃሚ ያላቸው ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መቋረጥን ተከትሎ ተጠቃሚዎች ሌሎች የማኅበራዊ አግልግሎት አማራጮችን በመፈለጋቸው በሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች ላይ መጨናነቅም ተፈጥሮ ነበር።

የፌስቡክ ምላሽ ምን ነበር?

የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ በተቀናቃኝ ማኅበራዊ ሚዲያ ትዊተር ላይ ሄዶ ለፌስቡክ አገልግሎት መቋረጥ ይቅር ለመጠየቅ ተገዷል።

የቴክኖሎጂ ተንታኙ ማይክ ፕሮላክስ ክስተቱ ፌስቡክ በቅርብ ዓመታት ሥርዓቶቹን በሙሉ ወደ አንድ ለማምጣት የወሰነበት ቴክኒነካዊ ሂደት ላይ ጥያቄ ያስነሳል ይላል።

ይህ የፌስቡክ ውሳኔ ወጪን የሚቀንስ ቢሆንም አንድ ችግር ሲያጋጥም ሁሉም ተያይዞ አብሮ ይጠፋል ይላል።

የፌስቡክ ኩባንያ አገልግሎቶች መቋረጥ ብዙ መስቅልቅልን ፈጥሮ ነበር። መረጃ ለማግኘት እና ከወዳጅ ዘመድ ለመገናኘት ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕን ብቻ የሚጠቀሙ ለሰዓታት ከዓለም ተቆራርጠው ነበር።

በተለይ ደግሞ በታዳጊ አገራት የሚገኙ ምርት እና አገልግሎታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሸጡ እና የሚያስተዋውቁ የበለጠ ተጎጂ ሆነው ነበር።

ከሁሉም በላይ ግን በአገልግሎቱ መቋረጥ እጅጉን የተጎዳው ፌስቡክ ኩባንያ ራሱ ነው።

ፌስቡክ ምን ያክል ገንዘብ አጣ?

ፌስቡክ አገልግሎቱ በመቋረጡ ለሰዓታት ማስታወቂያዎችን ማስኬድ አልቻለም ነበር። ይህም ገቢውን እና የገበያ ድርሻ ሽያጩ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል።

ፌስቡክ ለስድስት ሰዓታት ገደማ አግልግሎቶቹ በመቋረጣቸው ወደ 6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሲያጣ የገበያ ድርሻው ደግሞ ወደ 5 በመቶ ቀንሷል።