ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ ከእስር ተለቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Photo by Melody Sundberg
የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረገጽ መስራችና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ ከእስር ተለቀቀ።
ለሦስት ቀናት ያህል በእስር ላይ የቆየው ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ከደቂቃዎች በፊት ከእስር ቤት መውጣቱን ቢቢሲ ከጠበቃው እና ከእራሱ ከተስፋዓለም አረጋግጧል።
"ለማንኛውም ተፈትቻለሁ፤ ገና ከእስር ቤት ከወጣሁ ሦስት ደቂቃዎች ሆኖኛል" ሲል ተስፋዓለም ለቢቢሲ ዘጋቢ ተናግሯል።
በወቅቱም ከፖሊስ ጣቢያ ወጥቶ መኪና ውስጥ እየገባ ነበር።
ቅዳሜ ረፋድ ላይ በቁጥጥር ስር የዋለው ተስፋዓለም ሜክሲኮ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ዛሬ ቃሉን እንደሰጠ ቢቢሲ ከጠበቃው አቶ ሽብሩ በለጠ መረዳት ችሏል።
የጋዜጠኛውንም እስር ተክትሎ ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገቱት ኮሚቲ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (ሲፒጄ)ና ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደስ በአስቸኳይ እንዲፈታ በትናንትናው ዕለት ጠይቀው ነበር።
ተስፋዓለም በኢትዮጵያ ኢንሳይደር የማኅበራዊ ትስስር ገፁ በኢሬቻ በዓል ላይ፣ መስከረም 25፣ 2014 ዓ.ም የተነሳውን ተቃውሞ ቪዲዮዎች ከለጠፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በቁጥጥር ስር መዋሉን ሲፒጄ ገልጿል።
የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ በፌደራል ፖሊስ እጅ ስር እንደሚገኝ ለቢቢሲ አረጋግጠው ነበር።
ኃላፊው እንደተናገሩት ተስፋዓለም በአሁኑ ጊዜ "የፌደራል ፖሊስ የምርመራ ቢሮ የሜክሲኮ ማቆያ እንደሚገኝ" ገልጸው፤ "ምንም የሚፈጠር ነገር የለም። ያለውን ነገር እያጣራን ነው። ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የወንጀል ምርመራ ቢሮ ምክትል ኃላፊው፤ ጋዜጠኛ ተስፋዓለም በቁጥጥር ሥር ስለዋለበት ጉዳይ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ይህ ተግባር "መንግሥት በፕሬሱ ላይ ነፃ የሆነ ወይንም የተቃውሞ ሽፋንን ከማበረታት ይልቅ ለማፈን የሚያደርገው ተከተታይ ጥቃቶችን የሚያጋልጥ ነው" በማለት ሲፒጄ በትዊተር ገጹ አስፍሯል።
ሲፒጄ ፖሊስ ጋዜጠኛውን በአስቸኳይ እንዲፈታውም ጠይቋል።
ተስፋዓለም ከዚህ ቀደም በሽብር ወንጀል ከአንድ ዓመት በላይ መታሰሩን ድርጅቱ ጠቁሞ "የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደቀደመው ሚዲያው አፈና ስልቶች መመለሱ የሚያሳዝን ነው" ብሏል።
ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ በበኩሉ በትዊተር ገጹ በበዓሉ ላይ የተሰማውን ተቃውሞ ሲቀርጽ በቁጥጥር ስር የዋለው ተስፋዓለም በአስቸኳይ እንዲፈታ ኢትዮጵያ ባለስልጣናትን ጠይቋል።
"በአገሪቱ ውሰጥ የፀረ መንግሥት ተቃዋሚዎችን መቅረጽ ክልክል ነው? ከሥራው በስቀር ምንም አላደረገም። ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም" ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።
ተስፋዓለም ወደልደየስ ዜናና ትንታኔ የሚቀርብበት 'ኢትዮጵያ ኢንሳይደር' የተባለው ድረገጽ መስራችና ዋና አዘጋጅ ሲሆን፤ ገጹ በተለይ ወቅታዊ የፖለቲካ ዜናዎችን በማቅረብ እየታወቀ ያለ ከመሆኑ በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይም በርካታ ተከታዮችን በማፍራት ላይ ያለ ነው።
ቢቢሲ ከታማኝ ምንጮቹ መረዳት እንደቻለው ጋዜጠኛ ተስፋዓለም በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ መኖሪያ ቤቱ ላይ ፍተሻ መካሄዱን ገልጸዋል።












