በጃፓን በተጀመረው ፓራሊምፒክ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ምን ይጠብቃሉ?

የፎቶው ባለመብት, Walta
የቶኪዮ ፓራሊምፒክ ውድድር ማክሰኞ ነሐሴ 18/2013 ዓ.ም ተጀምሮ ለ13 ቀናት ይካሄዳል። በውድድሩ ኢትዮጵያ በሦስት አትሌቶች ትወከላለች።
ከተወዳዳሪዎቹ መካከል አንዱ የሆነው ታምሩ ከፍያለው ወደ ቶኪዮ ከማምራቱ በፊት ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ "ከተቻለ ወርቅ፤ ወርቅ ማግኘት ካልሆነም ከሦስቱ ሜዳልያዎች አንዱን ለአገሬ ይዤ እመለሳለሁ" ብሏል።
ኢትዮጵያን በቶኪዮ 2020 እንዲወክሉ ከተላኩ አንድ ወንድና አንድ ሴት አትሌቶች በተጨማሪ በዓለም አቀፉ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ (አይፒሲ) ግብዣ ውድድሩን እንደተቀላቀለ የገለጸው ታምሩ፤ "የአገር ማልያ ለብሶ ውድድሩን መካፈል በራሱ ትልቅ ነገር ነው" ሲል ስሜቱን ገልጿል።
ፓራሊምፒክ የሌሎች የአትሌቲክስ ውድድሮች ያህል ትኩረት እንደማይሰጠው አትሌቱ አያይዞ ተናግሯል።
"የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ የበጀት እጥረትና ሌሎች ችግሮች አሉበት። እንደሌሎች የአትሌቲክስ ዘርፎች በደንብ አልተሠራበትም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
ኢትዮጵያን የሚወክሉት ሦስት አትሌቶች ወደ ቶኪዮ በተሸኙበት ወቅት የተገኙት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ ፓራሊምፒክ እምብዛም ትኩረት እንዳልተሰጠው እንደገለጹ ታምሩ ተናግሯል።
ፕሬዝዳንቷ ሽኝት ሲያደርጉላቸው "በቀጣይ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ መሠራት አለበት" እንዳሉም አትሌቱ አክሏል።
የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ድረ ገጽ እንደሚጠቁመው ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓራሊምፒክ ውድድር የተሳተፈችው አስራኤል በቴል አቪቭ ላይ በተካሄደው የ1968 (እአአ) ውድድር ላይ ነው።
ከዚያም በ2012 ላይ በአትሌት ወንድዬ ፍቅሬ አማካይነት በፓራሊፒሚክ ውድድር ለአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው የብር ሜዳልያ ተመዝግቧል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የብር ሜዳልያ ያገኘችው በ2016 በሪዮ ደ ጄኔሮ የወንዶች 1500 ሜትር ሩጫ በአትሌት ታምሩ ደምሴ አማካይነት ነው።
የቶኪዮ ኦሊምፒክን ጨምሮ ኢትዮጵያ በፓራሊምፒክ ውድድር እስካሁን ስምንት አትሌቶችን አሳትፋለች።
አትሌት ታምሩ ለቶኪዮ ፖራሊምፒክ ውድድር ያለፈው በቱኒዚያ በተካሄደው የቶኪዮ ፓራሊምፒክ 1500 ሜትር ማጣሪያ ውድድር ላይ 03 ደቂቃ 56 ሰከንዶች በሆነ ሰዓት በመግባት ውድድሩን በአንደኝነት ማጠናቀቁን ተከትሎ ነው።
ሌሎቹ ኢትዮጵያን በፓራሊምፒክ ውድድር የሚወክሉት አትሌት ገመቹ አመኑ እና አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ናቸው።
ቲኒዚያ ላይ በ1500 ሜትር በተደረገው ውድድር አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ 4:31:53 በመግባት አንደኛ በመሆን አጠናቃለች።












