ኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የዓለም ሻምፒዮን 4ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች

በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ለአምስት ቀናት በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከዓለም አራተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቀቀች።
ኢትዮጵያ በድምሩ አስራ ሁለት ሜዳልያዎችን በማግኘት ነው አራተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ የቻለችው።
በዘንድሮው ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በሶስት ወርቅ፣ ሰባት ብር እና ሁለት የነሃስ ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች።
በደረጃ ሰንጠረዡ መሰረት ኬንያ፣ ፊንላንድንና ናይጄሪያ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።
ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ወርቅ ያገኘቸው በ3ሺህ ሜትር የወንዶች ሲሆን አንደኛ ሆኖ ማጠናቀቅ የቻለው ደግሞ አትሌት ታደሰ ወርቁ ነው።
ሌላኛው ኢትዮጵያን የወከለው አትሌት አሊ አብዱልመናን ደግሞ ታደሰን በመከተል ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል።
ታደሰ ወርቁ ውድድሩን 7 ደቂቃ 42 ሰከንድ ከ09 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት ነው አንደኛ ሆኖ ያጠናቀቀው።
በ800 ሜትር የሴቶች ውድድር ደግሞ አትሌት አያል ዳኛቸው በ2:02.96 በሆነ ሰዓት 1ኛ በመውጣት ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ ማስገኘት ችላለች።
አትሌት ሚዛን ዓለም በ16:05.61 በሆነ ሰዓት 1ኛ በወጣችበት የ5ሺህ ሜትር ሴቶች ውድድር ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ቁጥሯን ወደ ሶስት ከፍ አድርጋለች።

በ1500 ሜትር ወንዶች ውድድር የተሳተፋት አትሌት ወገኔ አዲሱ እና አትሌት መልኬነህ አዘዘ ደግሞ 2ኛ እና 3ኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የብር እና የነሀስ ሜዳልያዎችን አስገኝተዋል።
በ3ሺህ ሜትር አንደኛ መውጣት የቻለው አትሌት ታደሰ ወርቁ በወንዶች 5ሺህ ሜትር ፍፃሜ ውድድር ደግሞ 2ኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።
በሴቶች 3 ሺህ ሜትር ውድድር አትሌት መልክናት ውዱ የግል ምርጥ ሰዓቷን ጭመር በማስመዝገብ ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳልያ አግኝታለች።
በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያን በወከሉት አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ እና እመቤት ከበደ አማካይነት ሜዳልያ መመዝገቡን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በካሳራኒ ስታዲየም በተካሄደው የ5000 ሜትር የሴቶች ውድድር 2ኛ ደረጃን በመያዝ ካጠናቀቀች በኋላ የመሮጫ መስመርን ተላልፋለች በሚል ውጤቷ ውድቅ ተደርጎባት የነበረችው አትሌት መልክናት ውዱ የኢትዮጵያ የቴክኒካል ቡድን ያቀረበውን ቅሬታ ተከትሎ የብር ሜዳልያው እንደተመለሰላት ተገልጿል።












