ልዩ ፍላጎት፡ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የምልክት ቋንቋን የሥራ ቋንቋ ልታደርግ ነው

የምልክት ቋንቋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ከስዋሂሊ፣ ሊነጋላ፣ ኪቱባ እና ሽሉባ በተጨማሪ የምልክት ቋንቋን አምስተኛ የሥራ ቋንቋ ልታደርግ መሆኑ ተገለጸ።

በምልክት ቋንቋ የሚገለገሉ ሰዎች በቀላሉ መንግሥት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች እንዲያገኙ ለመርዳትም ቋንቋው በአገሪቷ ትምህርት ቤቶች በመደበኛ ትምህርት ይሰጣል ተብሏል።

የአገሪቷ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ሚኒስትር አሬን ኢሳምቦ "ልዩ ፍላጎት ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በሚገጥማቸው የተግባቦት ተግዳሮቶች ምክንያት ለረዥም ጊዜ ተገልለው ቆይተዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የምልክት ቋንቋ መምህር የሆኑት ኖኮላ ሺሎምባ እንዳሉት ከእነዚህ ዜጎች ህመማቸውን በትክክል መናገር አቅቷቸው የሞቱ አሉ። ሌሎች ደግሞ በተግባቦት ችግር ምክንያት በፍርድ ቤት ክርክር ተሸንፈዋል።

በአገሪቷ የተለያዩ ግዛቶች ያሉ የምልክት ቋንቋ ባለሙያዎች በትምህርት ቤቶች ውስጥ ወጥ የሆነ አቀራረብ እንዲኖር በሚጠቀሙባቸው ምልክቶች ላይ ለመስማማት ለአንድ ወር ያህል ለውይይት ይቀመጣሉ።

መንግሥት በበኩሉ የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላት ለማዘጋጀት አቅዷል።

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት የ2012 ሪፖርት ዲሞክራቲክ ኮንጎ ወደ ሁለት ሚሊየን የሚጠጉ ማየትና መስማት የተሳናቸው ዜጎች አሏት።