ካቢ ላሜ፡ ይህ ብዙዎች የሚያወሩለት የቲክቶክ ዓለሙ ኮከብ ማን ነው?

ካቢ ላሜ

የፎቶው ባለመብት, khaby.lame/tiktok/getty

ይህ የቲክቶክ የዓለም ፈርጥ እንደ ሌሎች ቢጤዎቹ በቲክቶክ ላይ ሲደንስ አይታይም። እንደውም ለዳንስ አካሉ እሺ ብሎ የሚታዘዝለት አይመስልም።

አይዘፍንም፤ ቃለ ተውኔት ጽፎ በመተወን ሌሎችን ቀልብ ለመሳብም አይጥርም።

የሌሎችን ድምጽና ትወና ለማስመሰል ደፋ ቀና ሲል አይታይም።

ዝም ብሎ የሰው ልጅን ውስብስብ ተግባራት ይተቻል፤ እንደ ዘበት።

በመላው ዓለም ካሉ የቲክቶክ ከዋክብት ሁሉ ከፍተኛ ቁጥር ካላቸው መካከል ሁለተኛው ነው።

100 ሚሊዮን ተከታዮች አሉት። ይህ ቁጥር ግን በአውሮፓ ብቻ ከታየ ቀዳሚ ያደርገዋል።

በቲክቶክ ላይ የሚለጥፋቸው ቪዲዮዎች ቀላል እና አጭር ናቸው።

የእርሱ ትችቶች በንግግር የተደገፉ አይደሉም፤ በቀላል ድርጊት የታጀቡ አንጂ።

ውስብስብ በሆነ መንገድ ቀላል ነገርን የሚከውኑ ሰዎችን ቪዲዮ በማሳየት፣ እርሱ ያንኑ ተግባር ቀላልና ግልፅ በሆነ መልኩ ያሳየዋል።

ከዚያን እጁን በማወናጨፍ እና አንገቱን በመነቅነቅ ያበቃል።

ካቢ ላሜ

የፎቶው ባለመብት, khaby.lame/tiktok

100 ሚሊዮን ተከታይ

ካቢ ላሜ በቲክቶክ የማኅበራዊ መገናኛ መድረክ ላይ ከቻርሊ ዲ አሚሊዮ በመቀጠል ከፍተኛ ቁጥር ተከታይ ያለው ወጣት ነው።

የቲክቶክ አካውንቱ ከ100 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች 1.3 ቢሊዮን ጊዜ ደግሞ ተወዶለታል።

ይህ ቁጥር በአገር ደረጃ ቢታይ በዩናይትድ ኪንግደም ከሚኖሩ ዜጎች በላይ ማለት ነው።

አንዳንዶች ካቢ የቻርሊን አንደኝነት ለመንጠቅ ይቻለዋል ሲሉ ይወራረዳሉ።

ይህ በዓለም ላይ ዝነኛ የሆነው ቲክቶከር ማን ነው? ለምን ዝነኛ ሆነ?

ካባኔ ላሜ በምዕራብ አፍሪካዋ አገር ሴነጋል ነው የተወለደው። አሁን ግን የሚኖረው ጣሊያን ውስጥ ነው።

የ21 ዓመቱ ወጣት ካቢ ቲክቶክን መጠቀም የጀመረው በመጋቢት ወር 2020 ነው፤ ኮሮናቫይረስ ዓለምን በተዋወቀበት ጊዜ እርሱ ቲክቶክን ተዋወቀ።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን ክፉኛ በደቆሰበት ወቅት እርሱም ከሚሰራበት ፋብሪካ ተሰናበተ። ካቢ በቀጥታ ወደ ቤተሰቦቹ አመራ።

ሌላ ሥራ ይፈልጋል ተብሎ ሲጠበቅ እርሱ ግን በየቀኑ ቲክቶክ ላይ ቪዲዮዎችን መለጠፍ ጀመረ።

ታዲያ ያኔ የቲክቶክ አካውንቱ ላይ ፈገግ የሚያሰኙ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ሲያጋራ እንዲህ በአንድ ጊዜ ስሜ በመላው ዓለም ይናኛል፤ ተግባሬ ብዙዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ብሎ ያሰበ አይመስልም።

ተንቀሳቃሽ ምስሎቹ የሚያተኩሩት እንዴት ሰዎች ያለምንም ተጨባጭ ምክንያት ነገሮችን እንደሚያወሳስቡ በማሳየት ነው።

እርሱ እንደሚለው በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎች የእርሱን ቪዲዮዎች የወደዱት ሳቅን በሚያጭረው የፊት ገጽታው የተነሳ ስለሚያስቃቸው ነው።

ሌላው ደግሞ የእርሱን ሃሳብ ለመረዳት ቋንቋ ማወቅ ወይንም መናገር ፈጽሞ አለመጠየቁ እንደሆነ ያስረዳል።

ካቢ የእግር ኳስ አድናቂ ሲሆን በቪዲዮዎቹ ላይ ስፖርት ክለብ ቲሸርቶችን ለብሶ ይታያል።

የጁቬንተስ ደጋፊ የሆነው ካቢ፣ ኤዲ መርፊ እና ዊል ስሚዝም ከሚያደንቃቸው የሆሊውድ ከዋክብት መካከል ናቸው።

በመላው ዓለም ቻርሊ ዲ አሚሊዮ ከ120 ሚሊዮን በላይ ተከታይ በመያዝ፣ ካቢ ላሜ ከ100 ሚሊዮን በላይ ተከታይ በማግኘት፣ አዲሰን ሬይ ከ80 ሚሊዮን በላይ እንዲሁም ዛክ ኪንግ ከ62 ሚሊዮን በላይ ተከታይ በመያዝ ቀዳሚዎቹ ቲክቶከሮች ናቸው።

ካቢ የቻርሊ ዲ አሚሊዮን ስፍራ በቅርቡ ይነጥቃል የሚል የበርካቶች ግምት ነው።

ከሐምሌ ወር አጋማሽ ወዲህ ከ20 ሚሊዮን በላይ ተከታዮችን በማግኘትም ቀዳሚ ሆኗል።

ቻርሊ ግን በዚሁ ተመሳሳይ ወቅት ያገኘው 2.6 ሚሊዮን ተከታይ ብቻ ነው።

ስለዚህ የካቢ ተከታዮች ቁጥር በዚሁ ፍጥነት ካደገ በቅርቡ የዓለማችን ቁንጮ ቲክቶከር ይሆናል ማለት ነው።