አብደላ ሐምዶክ ሱዳን ግዛቷን አስከብራ ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራት ፍላጎት አላት አሉ

የሱዳን የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር አብደላህ ሐምዶክ

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራት እንደምትፈልግ ነገር ግን ከወራት በፊት በወታደሮቿ ቁጥጥር ስር ያስገባችውን ኢትዮጵያ ይገባኛል የምትለውን ግዛት እንደምትጠብቅ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ወታደሮቻቸው ከወራት በፊት በቁጥጥራቸው ሥር ያስገቡትን እና ከኢትዮጵያ ጋር የሚወዛገቡበትን የድንበር አካባቢ በመጎብኘት መሠረተ ልማቶችን ሰኞ እለት ባስመረቁበት ጊዜ ነው።

የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣንት የሆኑት የወታደራዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በአወዛጋቢው ይዞታ ውስጥ ሱዳን ያስገነባቻቸውን መሠረተ ልማቶችን መመረቃቸው ተዘግቧል።

አልፋሽካ ውስጥ በሚገኘው ዋድ ኩሊ በተባለው መንድር ውስጥ በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ ባደረጉት ንግግር አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር "ጥሩ ግንኙነት" እንዲኖራት እንደሚፈልጉ ነገር ግን ግዛቷን እንደምትጠብቅና እንደምታስከብር መግለጻቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ኢትዮጵያና ሱዳን የግዛታቸው አካል እንደሆነ በመግለጽ ለረጅም ጊዜያት ሲነጋገሩበት የቆየው ለእርሻ ተስማማዊን የአልፋሽካ አካባቢ ከዘጠኝ ወራት በፊት የሱዳን ሠራዊት የኢትዮጵያ አርሶአደሮችን በማስወጣት በቁጥጥሩ ስር ማስገባቱ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ግዛቱ ወደነበረበት ተመልሶ ንግግር እንዲካሄድ በተደጋጋሚ ብትጠይቅም ከሱዳን በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ ይዞታውን በማጠናከር የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተገንብተውበታል።

የሱዳን ዜና ወኪል ሱና ጄነራል አል ቡርሐን በሥነ ሥርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ ቁጥጥር ሥር ቆይቶ ወደ ሱዳን በተካተተው የድንበር አካባቢ መረጋጋትና ደኅንነት እንዲሰፍን እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ዘግቧል።

ጄነራሉ ጨምረውም ሠራዊታቸውና ሕዝቡ ግዛቱ ወደ ሱዳን እንዲመለስ ላደረጉት ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸው፤ አካባቢው ለእርሻ ተስማማሚ የሆነ ለም መሬት በመሆኑ እያንዳንዱን ስንዝር መሬት ጠብቀው እንዲያለሙ ጥሪ ማቅረባቸውን ሱና ዘግቧል።

ኢትዮጵያና ሱዳን የሚዋሰኑበት የድንበር አካባቢ ሁለቱ አገራት በይገባኛል መቋጫ ሳያገኙለት ለዘመናት የቆየ ሲሆን ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች የሚገኙበት አካባቢ ነበር።

ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከአካባቢው መውጣቱን ተከትሎ የሱዳን ጦር ወደግዛቱ በመግባት ኢትዮጵያውያኑን አርሶአደሮች በማፈናቀል አካባቢውን መቆጣጠራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ድርጊቱን በመቃወም የሱዳን ጦር ከያዛቸው አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣና ጉዳዩ ችግሩ ቀደም ብሎ ተጀምሮ በነበረው ውይይት እንዲፈታ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም የሱዳን መንግሥት ሳይቀበለው ቀርቷል።