ኡጋንዳ በአሜሪካ ጥያቄ 2ሺህ የአፍጋኒስታን ስደተኞችን ልትቀበል ነው

ትናንት ከ600 በላይ የሚሆኑ የአፍጋኒስታን ዜጎች በአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ታጭቀው ከካቡል ወጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Defense One handout via Reuters

የምስሉ መግለጫ, ትናንት ከ600 በላይ የሚሆኑ የአፍጋኒስታን ዜጎች በአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ታጭቀው ከካቡል ወጥተዋል።

ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኡጋንዳ በአሜሪካ ጥያቄ 2ሺህ የአፍጋኒስታን ስደተኞችን ልትቀበል መሆኑ ተነገረ።

ታሊባን አፍጋኒስታንን መቆጣጠሩን ተከትሎ በርካቶች አፍጋኒስታንን ለቀው ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ትናንት እና ከትናንት በስቲያ አስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከአፍጋኒስታን ለመውጣት በመዲናዋ የሚገኘውን አየር ማረፊያ አጨናንቀው ታይተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሰዎች አውሮፕላን ለመሳፍር በሚያደርጉት ጥረት ከ8 ያላነሱ የአፍጋን ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል። ከእነዚህም መካከል በአውሮፕላን ተገጭተው እንዲሁም አውሮፕላን ላይ ተንጠልጥለው አውሮፕላኑ ከተነሳ በኋላ ወድቀው ሕይወታቸው ያለፉ ስለመኖራቸው በስፋት ተዘግቧል።

የኡጋንዳ የስደተኞች ጉዳይ ሚኒስትር ኢስተር አንያኩን ለቢቢሲ እንደገለፁት ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ስደተኞቹን በአሜሪካኖች ጥያቄ ለመቀበል ተስማምተዋል።

ይህ የሆነው በሳምንቱ መጨረሻ እጅግ ፈጣን የሆነው ታሊባን መስፋፋት እና የአፍጋኒስታን መንግሥት መውደቅን ተከትሎ ነው።

የመጀመሪያቹ 500 የሚጠጉ አፍጋኒስታን ዜጎች በኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በጥቂት ሰዓታት ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሚንስተሯ አክለውም ስደተኞቹ የኮቪድ ምርመራ እንደሚደረግላቸው እና ለይቶ ማቆያ እንደሚገቡ ተናግረዋል። ሁሉም ሎጂስቲክስ እና ወጪዎች በአሜሪካ መንግሥት ይሸፈናሉ።

ኡጋንዳ ከአፍጋኒስታን ወቅታዊ ቀውስ የሚሸሹ ሰዎችን በመቀበል የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ሀገር ትሆናለች።

ኡጋንዳ ስደተኞችን በማስተናገድ ረጅም ታሪክ አላት። በአሁኑ ጊዜ ከግጭቶች ወይም ከሌሎች አደጋዎች የሸሹ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች መኖሪያ ነች።

በኡጋንዳ የሚገኙ ስደተኞች ከሃገሪቱ ዜጎች ጎን በመንደሮች ወይም በመጠለያዎች ውስጥ ይኖራሉ። አንዳንዶቹ መሬት ተሰጥቷቸው እንዲሠሩም ተፈቅዶላቸዋል።

ታሊባን በከፍተኛ ፍጥነት በርካታ የአፍጋኒስታን አካባቢዎችን በመቆጣጠር ከትናንት በስቲያ እሁድ በመዲናዋ ካቡል የሚገኘውን ፕሬዝደንታዊ ቤተ-መንግሥት ወርሷል።

ነገሮች በፍጥነት በተቀያየሩባት አፍጋኒስታን፤ የአገሪቱ ፕሬዝደንትም አገር ጥለው ሸሽተዋል።

ታሊባን በጎርጎሮሲያዊያኑ 1990ዎቹ መጀመርያ በሰሜን ፓኪስታን ብቅ ያለ መደበኛ ያልነበረ እንቅስቃሴ ነበር።

እንደ ጎርጎሮሶዊያኑ 1998 ታሊባን የአፍጋኒስታንን 90 ከመቶ ይቆጣጠር ነበር። በዚያን ጊዜ ሕዝብ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነትን ማግኘት ችሎ ነበር።

ይሁን እንጂ አፍጋኒስታንን ሲያስስተዳድሩ የነበሩት ታሊባኖች እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ2001 በአሜሪካን አማካኝነት ሥልጣናቸውን አጥተው ነበር።

አሜሪካ ለ20 ዓመታት ከቆየችበት አፍጋኒስታን ጦሯን ማስወጣቷን ተከትሎ ታሊባን መላ አፍጋኒስታንን መልሶ በመያዝ ሥልጣን በእጁ ማስገባት ችሏል።