የእስራኤሉ ኩባንያ መተግበሪያ የ50ሺህ ታዋቂ ሰዎችን ስልክ መጥለፉ ተደረሰበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አንድ የእስራኤል ኩባንያ ለአምባገነን መንግሥታት በሚሸጠው የስልክ መጥለፊያ ሶፍትዌር የበርካታ ታዋቂ ሰዎች ስልክ ሲሰለል እንደነበረ ተደረሰበት።
ኩባንያው ሲሸጥ የነበረው ፔጋሰስ የሚባል መረጃ ቦርቧሪ (ስፓይዌር) ነው። ይህን መረጃ ቦርቧሪ መተግበሪያ የሚያመርተው ደግሞ በዓለም ዕውቅ የሆነው የእስራኤሉ ኤንኤስኦ ነው።
ዋንኛ ደንበኞቹ የአረብ አገራትና አምባገነን መንግሥታት ሲሆኑ ዜጎቻቸውን እና የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ለመሰለል ሲሉ ይህን የስልክ መረጃ ቦርቧሪ ስፓይዌር በመግዛት ደንበኞቹ ሆነው ዘልቀዋል።
የዚህ ድርጅት ደንበኞቹ ከሆኑት መካከል የአረብ አገራት ንጉሣዊያን ቤተሰቦች ይገኙበታል።
ሆኖም ሰሞኑን ሾልኮ በወጣ አዲስ መረጃ በዚህ ስፓይዌር አማካኝነት በትንሹ የ50ሺህ የዓለማችን ሥመ ጥር ሰዎች ስልክ መረጃ ሲጠለፍ እንደነበረ ተደርሶበታል።
መረጃቸው ሲጠለፍባቸው የነበሩ ሰዎችም ስም ዝርዝር ሚዲያዎች እጅ ደርሷል። ለጊዜው እነዚህ ስም ዝርዝሮች ሙሉ በሙሉ ይፋ አልተደረጉም።
የስፓይዌሩ አምራች በበኩሉ ጥፋቱ የኔ አይደለም ብሏል። ስፓይዌሩ ወንጀለኞችንና አሸባሪዎችን ለመከታተል ነው የተመረተው ሲል ማስተባበያ ሰጥቷል።
ፔጋሰስ ስፓይዌር አንድሮይድና አይፎን ስልኮችን ዘልቆ በመግባት፣ የድመጽ፣ የጽሑፍ፣ የቋት፣ የምሥል እና የተንቀሳቃሽ ምሥል እንዲሁም ዕለታዊ የስልክ ልውውጥ መረጃዎችን ልቅም አድርጎ በመውሰድ ለ3ኛ ወገን ያቀብላል።
የስልክ መረጃቸው ሲጠለፍባቸው ከነበሩ ሰዎች መካከል 180 የሚሆኑ ጋዜጠኞች ይገኙበታል። እነዚህ ጋዜጠኞች ለአልጀዚራ፣ ለኒውዮርክ ታይምስ፣ ለሲኤንኤን እና ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የሚሠሩ ናቸው።
በዚህ ዝርዝር ውስጥ ሳኡዲ በአሰቃቂ ሁኔታ ያስገደለችው የዋሺንግተን ፖስት አምደኛ ከማል ኻሾግጂ ጋር ይቀራረቡ የነበሩ ሁለት ሴቶች ስም ተገኝቷል።
እንዲሁም በሜክሲኮ በመኪና ማጠቢያው ውስጥ ተገድሎ የተገኘው ጋዜጠኛ ቢኔዳ ቢርቶ ጋር ወዳጅ የነበሩ ሰዎች ስም ተጠቅሷል።
ከዚህ በተጨማሪ የአገር መሪዎች፣ የንጉሣዊያን ቤተሰቦች፣ የግዙፍ ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ስልክ ተጠልፎ እንደነበረ ተደርሶበታል።
በቀጣይ ቀናት የየትኞቹ አገራት መሪዎች እና ታዋቂ ሰዎች ስልክ ተጠልፎ እንደነበር ስም ዝርዝር እንደሚወጣ ይጠበቃል።












