ትግራይ፡ኢትዮጵያ ወታደሮቿ በሰላም ማስከበሩ እንዳይሳተፉ መጠየቁ እንዳሳዘናት ገለፀች

የኢትዮጵያ ወታደሮች በመቀለ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትግራይ ጦርነት የተሳተፉ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ከሰላም አስከባሪነት ሊያግድ ይገባል በሚል የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀ መንበር መጠየቃቸው እንዳሳዘናት ኢትዮጵያ ገልፃለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ድጋፍ ሰጭ ዋና ኃላፈ አትዋል ካሬ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት ነው ይህንን ያሳወቁት።

የኮሚቴው ሊቀ መንበር ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ ለተመድ በጦርነቱ የተሳተፉ ወታደሮች ይታገዱ ብለው ደብዳቤ መፃፋቸው ከማሳዘን በተጨማሪ ሰላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ እያገለገሉ ያሉትን የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች አስተዋፅዖ ዕውቅና የነፈገ ነው ብለውታል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።

ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ በትግራይ ክልል ጦርነት የተሳተፉ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ አለመሳተፋቸው በአስተማማኝ የማጣራት ሂደት እስኪታወቅ ድረስ በተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ሥራዎች እንዳይሳተፉ በሚል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደብዳቤ መፃፋቸው የሚታወስ ነው።

በውይይቱ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል አዎንታዊ ሚና እንዲሁም የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የቆየ ታሪክን አጉልተው በማንሳት ተነጋግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት የአብዬ ጊዜያዊ የፀጥታ ኃይል (ዩኤንኢስፋ) የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሙትም በአብዬ ሰላምና እና መረጋጋትን ለማምጣት እጅግ ገንቢ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ቀጣይ ድጋፍ እንደምታደርግ ሚኒስትሩ ያረጋገጡ ሲሆን ዋና ኃላፊው በበኩላቸው አገሪቷ በተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ያላትን የተልዕኮ ሚናዋ አድንቀዋል።

ሴናተሩ ከሁለት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ወታደሮችን አስመልክቶ በፃፉት ደብዳቤ እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር በመሳሰሉ ገለልተኛ ተቋማት የማጣራት ሂደት እስኪታወቅ ድረስ እግዱ ሊፀና ይገባል በማለት መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።

በደብዳቤያቸው ላይ አክለውም ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወታደሮች የምታዋጣ እንደመሆኗ መጠን የተባበሩት መንግሥታት በሰላም ማስከበሩ ላይ የሚሳተፉ የኢትዮጵያ ወታደሮች በትግራይ ወታደራዊ ዘመቻ ላይ ስለመሳተፋቸው ጠንከር ያለ የማጣራት ሂደት እንዲከናወን መጠየቃቸውም ሰፍሯል።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ስር በተለያዩ አገራት ውስጥ ለሚደረጉ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች ከፍተኛ የሚባለውን ከ8 ሺህ 300 በላይ ሠራዊት ያበረከተች ሲሆን ከዚህም ውስጥ ከፍተኛው ቁጥር በሱዳን ውስጥ በሚገኙት ዳርፉርና በአብዬ ግዛት ውስጥ የተሰማሩ መሆናቸውም ይነገራል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) የስራ ድጋፍን በተመለከተ እንዲሁም በዳርፉርና (ዩናሚድ)፣ በአብዬና በደቡብ ሱዳን ያለውን የፀጥታ ኃይሉን የስራ ጊዜ መጠናቀቅ አስመልክቶ ኃሳቦችን መቀያየራቸውም ሰፍሯል።

ከዚህም በተጨማሪ ዋና ኃላፊው በኮቪድ-19 ወረርሽኝና ፈታኝ በሚባለው ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሳየውን አፈፃፀም አድናቆት ችረውታል ተብሏል።