የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ በደቡብ ሱዳን ላበረከተው አስተዋፅኦ በተባበሩት መንግሥታት ሜዳሊያ ተበረከተለት

የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በደቡብ ሱዳን

የፎቶው ባለመብት, UNMISS

የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ በደቡብ ሱዳን ላበረከተው አስተዋፅኦ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሽልማት ተበረከተለት።

605 አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ባታሊየን 1 አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል ሙሉጌታ ንጉሴ እንዳሉት "የመንገዱ ምቹ አለመሆንና ለግምት አስቸጋሪ የሆነው የፀጥታ ሁኔታ ተልዕኮውን በእጅጉ ፈታኝ አድርጎት ነበር" በማለት ወታደሮቻቸው የተሰጣቸውን ተልዕኮ በጥሩ ሥነ ምግባርና ሙያቸውን ባከበረ መልኩ ማከናወናቸውን ገልፀዋል።

ይህ የኢትዮጵያ ጦር ጁባ ከሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት መጠለያ ጎን ሰፍረው የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን ይጠብቅ ነበር። ጦሩ በመጠለያ ጣቢያው ዙሪያ ከጦር መሳሪያ ነፃ በሆነው ስፍራ እየተንቀሳቀሰ ጥበቃ ያደርግ የነበረ ሲሆን በከተማው መሀል ግጭቶች እንዳይከሳቱም መስራቱ ተገልጿል።

ሰላም አስከባሪው ኃይል ርቀው የሚገኙ ማህበረሰቦችን ለማግኘት የሚንቀሳቀሱትን በማጀብ፣ የፈራረሱ መሰረተ ልማቶችን የሚጠግኑ መሃንዲሶችን ከለላ በመስጠትና በሀገሪቱ ያምቢዮ ክፍለ ሃገር ተመድቦ ሰላም የማስከበር ሥራውን ይሰሩ ነበር ተብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ምክትል ፀሐፊ ተወካይ የሆኑት ሙስጠፋ ሶማሬ እንዳሉት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር በደቡብ ሱዳናዊያን ህይወት ላይ አዎንታዊ ለውጥ አምጥቷል። አክለውም ጦሩ ሰላም ለማስከበር በተሰማራበት ሁሉ መልካም ስም እንዳለው ገልፀው "ሰላም ለማስከበር በተሰማራችሁበት ስፍራ ያሉትን ከፍተኛ ተግዳሮቶች የተወጣችሁበትን ትጋታችሁን እና መሰጠታችሁን አደንቃለሁ" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በደቡብ ሱዳን

የፎቶው ባለመብት, UNMISS

ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ሰላም የማስከበር ተግባርን ከማከናወቷ ባሻገርም በተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲወርድ አስተዋፅኦ አድርጋለች።

በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ፍሰሃ ሻወል እንደተናገሩት "የደቡብ ሱዳን ሰላም የእኛም ሰላም ነው፤ የኢትዮጵያ ሰላም የደቡብ ሱዳናዊያን ሰላም ነው። በቀጥታ የሚገናኝ ነገር ነው። እዚህ እየሰራችሁ ያላችሁት ይህንን ነው። " በማለት የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰላም ማስከበሩ ጎን ለጎን በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም ለማስከበር በሚያደርገው ጥረት ውስጥ 8ሺህ ያህል ሠራዊት በማዋጣት ከቀዳሚዎቹ አንዷናት። ይህ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት በዓለም ዙሪያ ካሉት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች መካከል 8 በመቶ ያህሉ ነው።

ኢትዮጵያ ሴት የሰላም አስከባሪዎችንም በማዋጣትም ቀዳሚ ሃገር ናት።