የኢህአዴግ ጉባኤ የሁለተኛ ቀን ውሎ

11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ዛሬ ቀጥሎ የዋለ ሲሆን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሲወያይ ውሏል።
በአነስተኛ ቡድኖች እና በጋራ የተካሄዱት ውይይቶች በዋናነት በሁለት ጭብጦች ላይ ያተኮሩ እንደነበር ግንባሩን ወክለው ዛሬ አመሻሹን መግለጫ የሰጡት የፓርቲው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣አጋር ድርጅቶች እና የሲቪክ ማኅበራት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ፈቃዱ ተሰማ ገልፀዋል።አዲሱ መሪ ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ለፓርቲው ሊቀ -መንበር እና ለአገሪቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ብቅ ካሉ በኋላ በአገሪቱ የታዩት ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ የለውጥ እርምጃዎች ቀዳሚ የውይይት ርዕስ ሆነው በጉባዔተኛው ተነስተዋል ብለዋል አቶ ፍቃዱ።
ውይይቱን''ነፃ፣ ግልፅ እና የተሟሟቀ '' ሲሉ የገለፁት አስተባባሪው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ አመራር ከመጣ በኋላ እየታዩ ያሉ ለውጦችን "ህዝባዊ፣ ሕገ መንግሥታዊ እና ኢህአዴጋዊ" መልክ አላቸው ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥትን ጥሪ ተከትሎ ወደአገር መግባታቸውን፣ ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ሰላም መውረዱን፣ የፖለቲካ እስረኞች ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉን እንዲሁም ቀጠናዊ ትስስር ለመፍጠር ሂደት መጀመሩን ፓርቲው በጉባዔው እንደ ስኬት አይቷቸዋል።ጉባኤተኛው በዲሞክራሲ ምህዳር መስፋት እና የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል አስፈላጊነት ላይ መክሯል። ከዚህም በተጨማሪ በአስራ አንደኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ሪፖርት ላይ ሰፊ ውይይት እየተደረገ ነው ሲሉ አቶ ፈቃዱ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ኢህአዴግ ከዚህ በኋላ "የተደራጀ ሌብነት፣ ልግመኛነት ፣ ውጤት አልባነት እና ስርዓተ አልበኝነትን" አይታገስም በእነዚህ ጉዳዮች ላይም "ቀይ መስመር" አስምሯል ሲሉ ተናግረዋል።








