አራት ዓለም አቀፍ ተቋማት የአዲስ ስታንዳርድን ፍቃድ መታገድ ተቃወሙ

የአዲስ ስታንዳርድ መጽሔት እትሞች መካከል የአንዱ የፊት ገጽ

የፎቶው ባለመብት, Addis Standard

የምስሉ መግለጫ, የአዲስ ስታንዳርድ መጽሔት እትሞች መካከል የአንዱ የፊት ገጽ

የአዲስ ስታንዳርድ የበይነ መረብ ሚዲያ አሳታሚ የሆነው የጃኬን ሚዲያ የሥራ ፈቃድ መነጠቁን ተከትሎ የተለያዩ ተቋማት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በዚህም የአውሮፓ ሕብረት እንዲሁም ለጋዜጠኞች መብት የሚከራከሩት ሲፒጄ፣ አርኤስኤፍ እንዲሁም የአፍሪካው ኤፍፒኤ እርምጃውን ተቃውመዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ትላንት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ በሳፈረው ማብራሪያ "ተቋሙ የሽብርተኛ ቡድንን አጀንዳ ያራምዳል" በሚል የአዲስ ስታንዳርድ ፈቃድን ማገዱን አስታውቋል።

የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ ወኪል ቢሮ በትዊተር ገጹ "መገናኛ ብዙኃን ለማንኛውም የዴሞክራሲ ሥርዓት የደም ሥር ናቸው። ጋዜጠኞች በነጻነት ሥራቸውን መሥራታችው ወሳኝ ነው" ሲል እርምጃውን ተቃውሞ ጽፏል።

ዓለም አቀፉ የድንበር የለሽ ጋዜጠኞች ቡድን አርኤስኤፍ በበኩሉ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠው መጠየቁን ገልጿል።

ባለሥልጣኑ ውሳኔውን ግልጽ ባልሆነ መልኩ አሳልፏል ሲልም አክሏል።

"ጋዜጠኞችን ከሕግ አግባብ ውጪ ማሰር ይብቃ፤ ባለሥልጣናት የመገናኛ ብዙኃንን ነጻነት ማጥቃት ሊያቆሙ ይገባል" ሲልም አክሏል።

መቀመጫውን ናይሮቢ ያደረገው የአፍሪካ የውጭ ፕሬስ ማኅበር በበኩሉ ነጻ ሚዲያ ለዴሞክራሲ መጎልበት ከፍተኛ ሚና አለው ያለ ሲሆነ "የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ያለ ምንም ማብራሪያ የአዲስ ስታንዳርድን ፍቃድ መንጠቁ አስቆጥቶናል" ሲል ገልጿል።

የጋዜጠኞችን መብት ለመከላከል የተቋቋመው ሲፒጄ በበኩሉ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ስጥቷል።

አዲስ ስታንዳርድ ለዓመታት ጠንካራ ዘገባዎችን ብሎም ግለሰቦች ዕይታቸውን የሚያሰፍሩባቸው አስተያየቶችን በማቅረብ አማራጭ ሆኖ ቆይቷል ብሏል።

"ባለሥልጣናቱ በፍጥነት የአዲስ ስታንዳርድን ፈቃድ ሊመልሱ ይገባል። ጋዜጠኞቹ በነጻ ምኅዳር ውስጥ ሥራቸውን እንዲሠሩ ማስቻል ያስፈልጋል። ማንኛውም መገናኛ ብዙኃን ሥራውን ያለ ሳነሱር ብሎም ያለ ትንኮሳ ሥራቸውን እንዲሠሩ ማስቻል ይግባል" ሲል ተቋሙ ገልጿል።

የአዲስ ስታንዳርድን ፍቃድ የነጠቀው የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ስለእርምጃው በሰጠው ማብራሪያ ተቋሙ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ቡድን አጀንዳ ያራምዳል ሲል ወንጅሎታል።

"ይህም በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን ቡድን 'የመከላከያ ኃይል' ብሎ እስከመጥራት የደረሰ ነው" ሲል ገልጿል።

"ይህንን ጨምሮ ሌሎች ጥፋቶች ላይ ጥልቅ ምርመራ ይደረግበታል፤ እናም ተጨማሪ እርምጃዎች ይወሰዳሉ" ሲልም ባለሥልጣኑ አመልክቷል።

የአዲስ ስታንዳርድ መስራች ጸዳለ ለማ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውስድ ማሰባቸውን ገልጸዋል። "ምክንያቱም ይህ ትክክልለኛ ውሳኔ ነው ብለን ስለማናምን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ከሁለት የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ 15 ሰዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፤ ከቀናት በኋላ ሦስቱ ቢለቀቁም ቀሪዎቹ በእስር ላይ እንደሚገኙ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቆ ነበር።