አሜሪካ ከሩስያ ጋር ግንኙነት ባለው መረጃ መዝባሪ የተወሰደባትን ገንዘብ አስመለሰች

የፎቶው ባለመብት, Colonial Pipeline
ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈው ወር አንድ የበይነ መረብ መረጃ መዝባሪ ኮሎኒያል ፓይፕላይን ከተባለ ድርጅት ከወሰደው 4.4 ሚሊዮን ዶላር በርካታውን ማስመለሷ ተሰምቷል።
ዳርክሳይድ የተሰኘው የሳይበር ጥቃት አድራሽ ቡድን ምስራቅ አውሮፓ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ከሩስያ ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ ይጠረጠራል።
ይህ ቡድን ኮሎኒያል ፓይፕላይን የተባለውን ድርጅት ኮምፒውተር ሰርስሮ ገብቶ ለካሳ ክፍያ 4.4 ሚሊዮን ዶላር ወስዶ ነበር።
በዚህ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ላይ በደረሰው ጥቃት ምክንያት አሜሪካዊያን ለቀናት የነዳጅ እጥረት አጋጥሟቸው እንደነበር ይታወሳል።
ኩባንያው እንደሚለው በምስራቃዊ የሃገሪቱ ክፍል 45 በመቶ የሚሆነውን የዲዜል፣ ፔትሮልና የጄት ነዳጅ አቅርቦት ይሸፍናል።
የአሜሪካ መንግሥት ድርጅቶች ለመረጃ መዝባሪዎች በፍፁም የካሳ ክፍያ እንዳይሰጡ በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃል።
አሜሪካ ለመዝባሪዎች ገንዘብ መክፈል ማለት ወንጀልን የበለጠ ማበረታታት ማለት ነው ትላለች። ለዚህም ነው የሳይበር ደህንነታቸውን የበለጠ እንዲጠብቁ ለድርጅቶች ምክር የምትሰጠው።
የንግድ ሚኒስትሯ ጂና ሬይሞንዶ ባለፈው እሁድ በሰጡት መግለጫ ፕሬዝደንት ባይደን መሰል የሳይበር ጥቃቶችን ጉዳይ ከፑቲን ጋር በሚኖራቸው ስብሰባ ላይ ያነሳሉ ብለዋል።
የኮሎኒያል ፓይፕላይን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጆሴፍ ብላውት የአሜሪካ ፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ገንዘቡን ለማስመለስ ያደረገውን ጥረት አድንቀዋል።
ተንታኞች አሜሪካ ከሳይበር ጥቃት አድራሾች ገንዘብ ማስመለስ መቻሉ ትልቅ ስኬት ነው ይላሉ።
የአሜሪካ መንግሥት ገንዘቡን እንዴት እንዳስመለሰው በይፋ ያለው ነገር የለም። ነገር ግን የፍትህ ሚኒስቴር የወንጀለኛው ቡድን የቢትኮይን ዋሌት 'በኤፍቢአይ ቁጥጥር ሥር ነው' ብሏል።
ባለፈው ግንቦት ወር ጥቃት የደረሰበት ኮሎኒያል ፓይፕላይን ክፍያውን የፈፀመው በክሪፕቶከረንሲ ሲሆን በምትኩ የተቆለፈበትን ኮምፒውተር መክፈቻ የሚሆን ቁልፍ ተሰጥቶታል።
ነገር ግን ቁልፉ ወዲያው የተቆለፉትን ኮምፒውተሮች አልከፈተም ሲል ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።
የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የደረሰው የሳይበር ጥቃት አንዳንድ 'ሲስተሞች' ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን ኩባንያው ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ኪሳራ አድርሷል ብለዋል።
ዳርክሳይድ የመረጃ መዝባሪ ቡድን አባላት በወቅቱ ጥቃቱን ያደረሱት እነሱ እንደሆኑ በይፋ ተናግረው ነበር።
"ዓላማችን ገንዘብ ማግኘት እንጂ ማሕበረሰቡን ማሸበር አይደለም" ሲሉ ነበር ድረ-ገፃቸው ላይ የፃፉት።












