ባይደን የኮሮናቫይረስ መነሻ በአግባቡ እንዲመረመር አዘዙ

ባይደን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የደኅንነት ባለሥልጣናት የኮሮናቫይረስ መነሻን ለማወቅ የሚያደርጉትን ጥረት "እጅግ እንዲያጠነክሩ" አዘዙ።

የሚካሄደው ምርመራ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ነው ያፈተለከው የሚለውን መላ ምት ማጣራትም ያካትታል።

ባይደን እንዳሉት የደኅንነት አባላቱ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ያፈተለከ ነው በሚለው እና ከእንስሳት ወደ ሰው የተላለፈ ነው በሚሉት ሁለት መላ ምቶች ተከፋፍለዋል።

ፕሬዝደንቱ የደኅንነት ቡድኑ በ90 ቀናት ውስጥ የደረሰበትን እንዲያሳውቃቸው ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ቻይና፤ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ነው የወጣው የሚለውን መላ ምት አትቀበልም።

በአሜሪካ የቻይና ኤምባሲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ "ስም የማጥፋት ዘመቻውና ተጠያቂነትን ከራስ ማሸሹ በድጋሚ ተጀምሯል። ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ የወጣ ነው የሚለው የሴራ ትንተናም እንዲሁ" ብሏል።

ቫይረሱ በቻይናዋ ዉሃን ከተማ መጀመሪያ ላይ ከተከሰተ ወዲህ በዓለም ዙሪያ ከ168 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተይዘዋል። 3.5 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በተህዋሱ ምክንያት ሞተዋል።

ቫይረሱ ዉሃን በሚገኝ የአሣ መሸጫ ገበያ ውስጥ እንደተነሳ በማጣቀስ ሳይንቲስቶች ቫይረሱ ከእንስሳት ወደ ሰዎች መተላለፉን ገምተዋል።

ሆኖም ግን በቅርቡ በአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን የወጡ መረጃዎች ቫይረሱ ከቻይና ቤተ ሙከራ በድንገት እንዳመለጠ እየጠቆሙ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ላይ ሳሉ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ማይክ ፖምፔዮ እና ሌሎችም የአስተዳደሩ አባላት ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ስለማምለጡ በስፋት ይናገሩ ነበር።

መላ ምቱ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ማስረጃ ባይኖረውም፤ ቫይረሱ በቻይና ቤተ ሙከራ የተመረተው እንደ መሣሪያ ጥቅም ላይ ሊውል ነው ሲባልም ነበር።

ቻይና የቫይረሱን መነሻ ለማወቅ የሚደረገውን ምርመራ ካልደገፈች ቫይረሱ እንዴት እንደመጣ ለማወቅ ያስቸግራል።

ባይደን ሙሉና ግልጽ ምርመራ እንዲደረግ እያሳሰቡ ነው።

ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ያመለጠ ከሆነ በቻይና እና አሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት መሻከሩ አይቀርም።

ባይደን "ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ያመለጠም ይሁን ከእንስሳት ወደ ሰው የተሸጋገረ ምርመራ ሊደረግ ይገባል" ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከሁለቱ መላ ምቶች አንዱ ላይ የበለጠ ትኩረት ለማድረግ በቂ መረጃ እንደሌለም ተናግረዋል።

ስለዚህም የደኅንነት ባለሥልጣናቱ ማስረጃ ሰብስበው ተገቢውን ምርመራ እንዲያደርጉ አዘዋል።