አሜሪካ የኮሮናቫይረስ መነሻ 'በግልጽ' እንዲመረመር ጠየቀች

አሜሪካ የኮሮናቫይረስ መነሻ 'በግልጽ' እንዲመረመር አሳሰበች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 አመጣጥን በተመለከተ የሚያደርገው ቀጣይ ምርመራ 'ግልጽ' መሆኑን እንዲያረጋግጥ አሜሪካ ጠየቀች።

በሚኒስቴር ደረጃ በተደረገው የድርጅቱ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የአሜሪካው የጤና ሚንስትር ዣቪየር ቢሴራ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የኮሮናቫይረስ ምንጭ ምን እንደሆነ እንዲገመግሙ ሊፈቀድላቸው ይገባል ብለዋል።

የአሜሪካ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ቫይረሱ ቻይና ከሚገኝ ቤተ ሙከራ ስለማፈትለኩ የሚያሳዩ መረጃዎች እየጨመሩ ነው።

ኮቪድ-19 በማዕከላዊ ሁቤይ አውራጃ በምትገኘው ውሃን ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ እአአ በ2019 ተገኝቷል።

ከዚያን ወዲህ በዓለም ዙሪያ ከ167 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከ3.4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ሕይወታቸው ማለፉ ሪፖርት ተደርጓል።

በመጋቢት ወር የዓለም የጤና ድርጅት ከቻይናውያን ሳይንቲስቶች በኮቪድ-19 አመጣጥ ላይ በጋራ ባቀረቡት ዘገባ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ የመነሳት ዕድሉ "እጅግ በጣም የማይታሰብ ነው" ብለው ነበር። ሆኖም የዓለም ጤና ድርጅት ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልገው አስታውቋል።

ነገር ግን ጥያቄዎች እንደቀጠሉ ናቸው። ከአሜሪካ የስለላ ምንጮች ጋር የሚያያዙ ሪፖርቶች እንደሚሉት ቻይና በማኅበረሰቡ ውስጥ አዲሱ በሽታ መኖሩን ይፋ ከማድረጓ ከሳምንታት በፊት የዉሃን ቫይረሶች ምርም ተቋም ሦስት አባላት ሆስፒታል ገብተው ነበር።

ቤይጂንግ በተደጋጋሚ ሪፖርቶቹን ውድቅ ያደረገች ሲሆን ይልቅም ቫይረሱ ከአሜሪካ ቤተ ሙከራ የመጣ ሊሆን ይችላል ስትል ደጋግማ ትናገራለች።

የአሜሪካ የጤና እና ሰብዓዊ አገልግሎት ሚንስትሩ ዣቪየር ቤሴራ፤ ማክሰኞ ለዓለም ጤና ድርጅት ባደረጉት ንግግር ቻይናን በስም አልጠቀሱም። ነገር ግን አሜሪካ ከቀጣዩ ምርመራ ጥብቅ አካሄድ እንደምትጠብቅ ግልጽ አድርገዋል።

በድርጅቱ በተዘጋጀው የዓለም የጤና ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግርም "የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከሕይወታችን አንድ ዓመት መውሰድ ብቻ ሳይሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳጥቶናል" ብለዋል።

አክለውም "የቫይረሱን አመጣጥ የሚመለከተው የምዕራፍ 2 ጥናት ግልጽ፣ ሳይንስን መሠረት ያደረገ እና ለዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የቫይረሱን ምንጭ እና የወረርሽኙን የመጀመሪያ ቀናት ሙሉ በሙሉ የመገምገም ነፃነት የሚሰጥ መሆን አለበት" ብለዋል።

ዋይት ሐውስ ማክሰኞ ዕለት ከዓለም የጤና ድርጅት "ከጣልቃ ገብነት ወይም ከፖለቲካዊ ወገንተኝት የፀዳ የወረርሽኙን አመጣጥ በባለሙያ የሚመራ ግምገማ" እንደሚጠብቅ ገልጿል።

የብሔራዊ የአለርጂ እና ተላላፊ በሽታዎች ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር እና የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የህክምና ዋና አማካሪ አንቶኒ ፋውቺ ቫይረሱ ከእንስሳት ወደ ሰው ተላልፏል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

በዚህ ወር ግን ኮቪድ-19 በተፈጥሯዊ መንገድ ስለመጀመሩ ሙሉ ለሙሉ እርግጠኛ አለመሆናቸውን አስታውቀዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቫይረሱ መነሻ የዉሃን የቫይሮሎጂ ተቋም እንደሆነ ከተናገሩ በኋላ ቫይረሱ ከቤተ ሙከራ ነው የወጣው የሚለው የሴራ ትንተና ውድቅ ተደርጓል። አብዛኛዎቹ የአሜሪካ የመገናኛ ብዙሃን እንደዚህ ያሉትን ጥያቄዎች ሐሰት ሲሉ ገልጸዋል።

ማክሰኞ ትራምፕ ለኒው ዮርክ ፖስት በተላኩት ኢሜል ባለቤትነቱን ለመውሰድ ፍላጎት አሳይተዋል። "ይህ ከመጀመሪያ ጀምሮ ለእኔ ግልጽ ነበር። ግን እንደተለመደው በጣም ብዙ ተነቅፌበታለሁ። አሁን ሁሉም 'እሱ ትክክል ነበር' ይላሉ" ብለዋል።