ቻይና ለዩናይትድ ኪንግደም እቃዎችን በማቅረብ ጀርመንን በለጠች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በምትልካቸው ቁሳቁሶች ብዛት ጀርመንን በለጠች።
የንግድ ልውውጥ መመዝገብ ከጀመረ አንስቶ ባልታየ ሁኔታ ቻይና ለዩናይትድ ኪንግደም እቃ በመላክ ግንባር ቀደም አገር ሆናለች።
የብሔራዊ ስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው በዚህ ዓመት የመጀመሪያው ሦስት ወራት ከቻይና የተላኩ ቁሳቁሶች በ16.9 ቢሊዮን ዩሮ ይገመታሉ። ይህም እአአ በ2018 ከነበረው የ66 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በአንጻሩ ከጀርመን የሚላኩ እቃዎች ወደ 12.5 ቢሊዮን ዩሮ ወርደዋል።
ይህ የንግድ አጋር ለውጥ የመጣው ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ከአውሮፓ ሕብረት መውጣቷን ተከትሎ ነው። ከብሬግዚት ወዲህ የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት የንግድ ትስስር ላልቷል።
ከዚህ ባሻገር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የቻይና ቁሳቁሶች ተፈላጊ እንዲሆኑ ግድ ብሏል።
የብሔራዊ ስታትስቲክስ ተቋም ብሬግዚት እና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዩኬ ንግድ ላይ ያሳደሩትን ተጽዕኖ ፈትሿል።
የዩኬ እና የአውሮፓ ሕብረት አዲስ አይነት ግንኙነት የንግድ ትስስራቸውን እንዳላላው የሚጠቁም ማስረጃ ተገኝቷል።
ከጀርመን ወደ ዩኬ የሚላኩ ቁሳቁሶች ቁጥር የቀነሰው እአአ ከሚያዚያ 2019 ወዲህ ነው። ይህ ወቅት ዩኬ ከአውሮፓ ሕብረት ስለምትወጣበት መንገድ ጥያቄዎች የነበሩበት ነው።
በሌላ በኩል የጀርመን መኪና አምራቾች በወረርሽኙ ሳቢያ ገበያቸው ተቀዛቅዟል።
በዩኬ የመኪና ማሳያ መደብሮች በወረርሽኙ ሳቢያ በመዘጋታቸው አዲስ መኪና ለመግዛት ያለው ፍላጎት አሽቆልቁሏል።
ዩኬ ከአውሮፓ ሕብረት ከወጣች ወዲህ ከአየርላንድ ጋር የነበራት የንግድ ትስስርም እንቀድሞው አልሆነም።
ቀድሞ ዩኬ መገልገያዎችን ትልክላቸው ከነበሩ አምስት ግንባር ቀደም አገራት አንዷ አየርላንድ ነበረች።
በዘመናዊ መንገድ የንግድ ልውውጥ ምዝገባ የተጀመረው እአአ በ1997 ነው።
ከዚያ ዘመን አንስቶ ጀርመን ለዩኬ እቃ በመላክ ቁጥር አንድ አገር ነበረች። በእርግጥ 2000 ላይ ለስድስት ወራት ያህል ይህንን የአንደኝነት ቦታ አሜሪካ ወስዳው ነበር።
ዩኬ ከአጠቃላይ የአውሮፓ ሕብረት አገራት ጋር ታደርግ የነበረው ንግድ 23.1 በመቶ ቢቀንስም፤ አሁንም የዩኬ ዋነኛ የንግድ አጋሮች የሕብረቱ አባል አገራት ናቸው።
ከቻይና ወደ ዩኬ ከሚገቡ መገልገያዎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እና የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ናቸው።
ባለፈው ዓመት፤ ቻይና ከዓለም አገራት ቀድማ ወረርሽኙን ማሸነፏን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ንግዷ ያደገ ቀዳሚዋ አገር ናት።












