የማሊን መፈንቅለ መንግሥት የመራው ኮሎኔል በድጋሚ ሥልጣን በኃይል ያዘ

ኮሎኔል አስሚ ጎይታ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ኮሎኔል አስሚ ጎይታ

በማሊ ከዓመት በፊት መፈንቅለ መንግሥት የመራው ኮሎኔል አስሚ ጎይታ ሥልጣን በድጋሚ በኃይል ያዘ።

ኮሎኔሉ ሥልጣኑ በእጁ መልሶ ያስገባው የአገሪቱን ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቁጥጥር ሥራ አውሎ ካሰራቸው በኋላ ነው።

የባለፈው ዓመት የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ኮሎኔል አስሚ ጎይታ የሽግግሩ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኖ ሲያገለግል ነበር።

ሆኖም ባልተጠበቀ ሁኔታ ፕሬዝዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነታቸው አልተወጡም በሚል አስሯቸዋል።

ኮሎኔሉ እንደሚለው ፕሬዝዳንት ባህ ንዳው እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞክራት ኦውኔ የሽግግር መንግሥቱን ሥራ ሲያጓትቱና በሥራም ሲለግሙ ነበር።

ሁለቱ መሪዎች የታሰሩት የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ሁለት ከፍተኛ መኮንኖችን በሌላ ከተተኩ ከሰዓታት በኋላ ነበር።

ኮሎኔል ጎይታ ምርጫው በሚቀጥለው ዓመት በተያዘለት ጊዜ ይካሄዳል ብሏል። ሕዝቡም እንደ ወትሮው ያለ ምንም ሐሳብና ጭንቀት ወደ ሥራው እንዲሰማራ አዟል።

ሆኖም ያሰራቸውን ፕሬዝዳንቱንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአስቸኳይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በአፍሪካ ኅብረት፣ በኢኮዋስ፣ በአውሮፓ ኅብረት እንዲሁም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የቀረበለትን ጥያቄ ቸል ብሎታል።

ፕሬዝዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዋና ከተማዋ ባማኮ ወጣ ብሎ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ መታሰራቸው ተመላክቷል።

የወታደራዊ ቡድኑ መሪ ኮሎኔል ጎይታ ባለፈው ዓመት የመራውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ የ18 ወራት የሽግግር ምክር ቤት ተሰይሞ ነበር።

በዚህ ምክር ቤት ውስጥ ሥልጣን ሊይዙ የሚችሉት ከሠራዊቱ ውጭ ያሉት ናቸው በሚል ኢኮዋስ ሲወተውት ቆይቷል።

ባለፈው ዓመት ይኸው ኮሎኔል ጎይታ የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ኬይታን ከሥልጣን በኃይል ሲያስወግድ የአገሪቱ ነዋሪዎች በደስታ አደባባይ ወጥተው ነበር።

ሆኖም ባለፉት 9 ወራት የታየው አዝጋሚ የለውጥ ሂደት ዜጎችን ቅሬታ ውስጥ ከቷቸው ነበር። የሠራተኛው ማኅበር የጠራው የሥራ ማቆም አድማም የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ማሽመድመድ ይዞ ነበር።

ይህን ተከትሎ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሹም ሹር በማድረጉ ኮሎኔል ጎይታ ቅሬታ አድሮበት ነው እርምጃውን የወሰደው ተብሏል።

አሁን የኢኮዋስ ልዑክ ባማኮ በመግባት የወታደራዊውን ቡድን መሪ ለማግባባት ይሞክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው ዓመትም መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ ኢኮዋስ በዚያች አገር ማዕቀብ እጥላለሁ በማለቱ ነበር የሽግግር መንግሥት መመሥረት የተቻለው።

በአገሪቱ እጇ ረዥም ነው የምትባለውና ማሊን ለዓመታት በቅኝ የገዛችው ፈረንሳይ፤ የአውሮፓ ኅብረት ማዕቀብ እንዲጥል አስደርጋለሁ ስትል ዝታለች።

የባሕር በር አልባዋ ማሊ በአፍሪካ ድሃ አገራት ተርታ የምትመደብ ሲሆን የአገሪቱ በርካታ አካባቢዎች ልማት የማያውቃቸው ናቸው።