ሱዳን በሰሜን ምሥራቅ ግዛቷ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገገች

የሱዳን ካርታ

በሱዳን ሰሜን ምሥራቅ ግዛት ውስጥ በተከሰተ የጎሳ ግጭት ሳቢያ የደረሰ ጉዳትን ተከትሎ በአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ።

የአገሪቱ መንግሥት ዜና ወኪል የሆነው ሱና እንደዘገበው በፖርት ሱዳን ግዛት ውስጥ በተከሰተው ግጭት አምስት ሰዎች ሲገደሉ 13 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ችግሩ የተከሰተበት የሬድ ሲ ግዛት አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ስለደረሰው ጉዳት ምንም አይነት ዝርዝር መግለጫ አስካሁን አልሰጠም።

በዚህም ሳቢያ የአገሪቱ የቀይ ባሕር ተዋሳኝ ግዛት በሆነችው በፖርት ሱዳን ከተማ የተከሰተውን ግጭት ለመቆጣጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገ ሲሆን የምሽት የሰዓት እላፊ ገደብም ተጥሏል።

የአካባቢው የደኅንነት ኮሚቴ ስላጋጠሙት ሁኔታዎች እንደመረመረና የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ያላቸውን አስፈላጊ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን የሱና ዘገባ አመልክቷል።

ሱና በዘገባው ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት ስለሆነው ግጭት መንስኤ የሰጠው ዝርዝር የለም።

ነገር ግን የአካባቢውን ጸጥታ የሚከታተለው ኮሚቴ ነዋሪዎች የሚናፈሱ አሉባልታዎችን እንዳይሰሙና ማኅበራዊ ትስስሩንና ሰላሙን እንዲጠብቁ ጥሪ ማቅረቡን ገልጿል።

ሱዳን ከቀይ ባሕር ጋር የምትዋሰንበት ግዛት በሆነው ምሥራቃዊ ክፍሏ ውስጥ በምትኘው የወደብ ከተማዋ ፖርት ሱዳን ውስጥ ባለፈው ሳምንት የተከሰተውን ግጭት ለመቆጣጠር እርምጃ እየወሰደች መሆኑ ተነግሯል።

ሬድ ሲ ለተባለው የሱዳን ሰሜን ምሥራቅ ግዛት በጎሳዎች መካከል የሚከሰት ደም አፋሳሽ ግጭት አዲስ ክስተት አይደለም።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው ባሉ የቤኒ አሚርና ኑባ ማኅበረሰቦች መካከል ተደጋጋሚ ከባድ ግጭቶች ማጋጠማቸው የተነገረ ሲሆን፤ ከሁለት ዓመት በፊት ጎሳዎቹ አለመግባታቸውን በዘላቂነት ለመፍታት በመሪዎቻቸው አማካይነት ስምምነት ላይ ቢደርሱም ግጭቱ ቀጥሏል።