ኢትዮጵያ የውጭ አገር ዘጋቢዎች በአገሪቷ ሕግ እንዲመሩ አሳሰበች

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Media Authority
ኢትዮጵያ በአገሪቱ ተቀማጭ የሆኑ የውጭ አገር ዘጋቢዎች በሥራ ፈቃድ የተጣለባቸውን ግዴታ እንዲያከብሩና በአገሪቷ ሕግ እንዲመሩ አሳሰበች።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ላይ የውጭ አገር ዘጋቢዎች ዓለም አቀፍ እሴቶችን በመከተል፣ ሙያቸውን ባከበረ መልኩና የአገሪቷን ሕጎች በተከተለ መልኩ እንዲሰሩ አሳስቧል።
ነገር ግን የሕግ ጥሰቶች በሚያጋጥሙበት ወቅት "እንደ ማንኛውም አገር ሕግ የማስከበር ግዴታ አለብን" ብሏል መግለጫው።
መግለጫው በምን መልኩ ሕግ እንደሚያስከብር ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
በግጭት አዘጋገብ ወቅት የጋዜጠኝነት መርሆችን እንዲያከብሩ ያሳሳበው ባለሥልጣኑ አገሪቱ ወታደራዊ ዘመቻዎች በምታካሂድባቸው ቦታዎች ዘጋቢዎች መግባት የሚችሉበት ቦታ ውስን ነው ብሏል።
የግጭት ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ክፍት አለመሆን (መታገድ) በሌሎች አገራት ላይ በመሰረታዊነት የሚሰራበት መሆኑን ያስታወሰው መግለጫው፤ እነዚህ ጋዜጠኞች የአገሪቱን ሕጎች አክብረው የሚሰሩና በሥራ ፈቃዳቸው የተጣለባቸውን ግዴታ የሚያከብሩ ከሆነ መስሪያ ቤቱ በትብብሩ ይቀጥላል ብሏል።
አገሪቷ የዓለም አቀፍ አስራሮችን በሚከተሉ መለኪያዎች መሰረት ትብብር እንደምታደርግና በተቻለም መጠን በነዚህ ቦታዎች ተገኝተው ሪፖርት እንዲያደርጉ እንደሚያመቻች አስታውሷል።
በአገሪቷ ውስጥ 35 የሚሆኑ የውጭ አገር ሚዲያዎችና 129 የሚሆኑ ዘጋቢዎቻቸው የሥራ ፈቃድ አግኝተው እየሰሩ መሆኑ ተገልጿል።
በተለይም ከትግራይ ክልል ካለው ግጭት ጋር በተያያዘ 82 የሚሆኑ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ጋዜጠኞች ወደ ክልሉ ሄደው እንዲዘግቡ ጊዜያዊ ፈቃድ መሰጠቱንም አስታውሷል።
ኢትዮጵያ በሕገ መንግሥቷ የተቀመጠውን የፕሬስ ነፃነት፣ የመናገር ነፃነትና፣ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት ለማስከበር የመንግሥት ቁርጠኝነት እንዳለው የገለፀው መግለጫው ይህም በተግባር የተፈተነ ነው ብሏል።
በባለፉት ሦስት ዓመታት መንግሥት የፕሬስ ምህዳሩን ለማስፋት እርምጃዎችን የወሰደ እንደሆነ ያስታወቀው መግለጫው ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ይጠቀሳል ብሏል።
ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ አገሪቱ በሚዲያው ዘርፍ ባሳየችው መሻሻል ብትወደስም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ከፕሬስ ነፃነት ጋር ተያይዞ ስሟ በአሉታዊ መንገድ መጠቀሱ አልቀረም።
በባለፈው ሳምንት የኒውዮርክ ታይምስ ኢትዮጵያ ዘጋቢ ሳይመን ማርክስ ከአገር መባረሩን ተከትሎ በሚዲያ ነፃነት ላይ የሚሰሩ ተቆርቋሪዎች አውግዘውታል።
ከእነዚህም መካከል ለጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ አንዱ ነው።
"ሳይመን ማርክስን ያለምንም ማስጠንቀቂያም ሆነ ማብራሪያ ለማባረር መወሰኗ አገሪቷ በትግራይ ላይ ያለውን የጦርነት ትርክት ለመቆጣጠር እንዲሁም ለሂሳዊ ዘገባዎች ታጋሽ አለመሆንን ያጋለጠ ነው" ሲሉ የሲፒጄ ሰሃራን በታች አገራት ተወካይ ሙቶኪ ሙሞ በመግለጫቸው ወቅሰዋል።
የጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ሳይመን ማርክስ የሥራ ፈቃዱ ተመልሶ ወደ አገር እንዲመለስ የጠየቀው መግለጫው፤ አገሪቷ በቅርቡ ለምታደርገው ምርጫ የአገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች በነፃነት የሚሰሩበት መድረክ ሊመቻችላቸው ይገባል ብሏል።
የጋዜጠኛውን መባረር አስመልክቶ ሲፒጄ ብቻ ሳይሆን ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድንም አገሪቷ "ወደቀደመ መጥፎ ተግባሯ እየተመለሰች ነው" ሲል አውግዟል።
ጋዜጠኛው ከኢትዮጵያ "ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ በማቅረቡ" ከአገር መባረሩን የመንግሥት ባለስልጣናትን ዋቢ አድርጎ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
አየርላንዳዊው ጋዜጠኛ ከአገር ከመባረሩ በፊት ባለስልጣናቱ ጠርተው እንዳናገሩትና ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ወስደው ለስምንት ሰዓታት ያህል በቁጥጥር ስር አውለውት እንደነበር አስታውቋል።
ባለስልጣናቱ ከአገር እንዲወጣ ስለተደረገበት ምክንያት ምንም አይነት ማብራሪያ አልተሰጠኝም ያለው ጋዜጠኛ ወደ ቤቱ ሄዶ ጓዙን እንዳይሸክፍ እንዲሁም ልጁን እንዳይሰናበት መከልከሉን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ሐሰተኛ ዘገባዎችን በመጥቀስ የጋዜጠኛው ፈቃድ የሰረዙት ሚያዝያ 29/2013 ዓ.ም ነበር፤ እስከ ጥቅምት ድረስም እንደማይታደስ ለጋዜጠኛው መንገራቸውን የኒውዮርክ ታይምስ ሪፖርት አመላክቷል።
ጋዜጠኛው ያለ ሥራ ፈቃድ በአገር ውስጥ መቆየት እንደማይችል አሶሺየትድ ፕሬስ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ኃላፊ መሃመድ ኢድሪስን ዋቢ አድርጎ አስነብበቧል።
ለሁለት ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ የቆየው ጋዜጠኛው በተለይም በትግራይ ባለው ጦርነት በኢትዮጵያና በኤርትራ ወታደሮች የተፈፀመው የመብት ጥሰቶችን፣ ግድያዎችንና መደፈሮችን ላይ በርካታ ዘገባ መስራቱን ኒውዮርክ ታይምስ በዘገባው አስነብቧል።
ጋዜጠኛው በኢትዮጵያ ላይ የሰራው ዘገባ "ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጫና እንደፈጠረና" የፕሬስ ፈቃዱን የመሰረዝ ውሳኔውም የመጣው ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት መሆኑንም ጋዜጠኛው መናገሩን ኒውዮርክ ታይምስ በዘገባው አስፍሯል።
የትግራይ ጦርነት ከተከሰተ በኋላ ቢያንስ 10 ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር ያስታወሰው የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ፤ ከነዚህም ውስጥ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎቹ ቢቢሲ፣ ሮይተርስና ሎስ አንጀለስ ታይምስ ዘጋቢዎች እንደሚገኙበት ጠቅሷል።
ከዚህም በተጨማሪ አልጀዚራና ሎስ አንጀለስ ታይምስን ጨምሮ ለተለያዩ ሚዲያዎች የምትሰራ ኢትዮጵያዊት ጋዜጠኛ ሉሲ ካሳ ሦስት የታጠቁ ሰዎች ቤቷን ሰብረው ገብተው እንደፈተሹ፣ ጥያቄዎች እንዳቀረቡላትና የዘገባ ቁሳቁሶቿን እንደወሰዱ ሲፒጄ ጋዜጠኛዋን ዋቢ አድርጎ በየካቲት መግለጫው አውጥቷል።
ጋዜጠኛው ከፍተሻው በፊት በፊት ለሎስ አንጀለስ ታይምስ የትግራይ ሴቶች በኤርትራ ወታደሮች የተፈፀማቸውን የቡድን መደፈር በማጋለጥ ፅፋ ነበር በማለት ሲፒጄ አስታውሷል።
በየካቲት ወር ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ መግለጫ የሉሲ ቤት ተሰብሮ ስለመገባቱ ምንም ባይልም ጋዜጠኛዋ ከኢትዮጵያ የብሮድካስት ባለስልጣን ፈቃድ እንደሌላት አስታውቋል።








