'ኤርትራ ለቅኝ ግዛትና ለባርነት አልተንበረከከችም' ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

ኤርትራ 30ኛ ዓመት የነጻነት ክብረ በዓል እያከበረች ትገኛለች።

የፎቶው ባለመብት, Yemane G Meskel

ኤርትራ 30ኛ ዓመት የነጻነት ክብረ በዓሏን ሰኞ ግንቦት 16/2013 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ አክብራለች።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተለይታ ነጻ አገር ከሆነችበት ጊዜ አንስቶ አገሪቱን ለሦስት አሥርት ዓመታት በበላይነት የመሩት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ ክብረ በዓሉን አስመልክተው ባደረጉት ንግግር፤ "አገሪቱ ለባርነት፣ ለቅኝ ግዛት፣ ኃይል ለተሞላው ግዞት እና ማታለል አልተንበረከከችም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ኤርትራ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር እንዲሁም ፈተናዎችን ለማለፍ ያላትን አቅም አሞግሰዋል።

"ያለማቋረጥ ግጭት በማጫር ኤርትራን በግዞት ስር ለማቆየት የሞከሩ ኃይሎች ነበሩ" ሲሉ ቢወቅሱም፤ በንግግራቸው ያነሷቸው ኃይሎች የትኞቹን እንደሆነ በግልጽ አላስቀመጡም።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከ20 ዓመታት በፊት የገቡበት የድንበር ጦርነት የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈ ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በሁከቱ አገራት መካከል የነበረውን ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ሁኔታ ለውጠው ከኤርትራ መንግሥት ጋር ሰላም በማውረዳቸው እአአ በ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት ማግኘታቸው ይታወሳል።

ኤርትራ 30ኛ ዓመት የነጻነት ክብረ በዓል እያከበረች ትገኛለች።

የፎቶው ባለመብት, Yemane G Meskel

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባደረጉት ንግግር "ለ20 ዓመታት ሉዓላዊ ግዛታችን ሲያዝ መታገሳች አሁን ውጤት አምጥቷል" ብለዋል።

ባለፈው ጥቅምት ወር በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ውስጥ በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነት ሲቀሰቀስ፤ ኤርትራ ሚሳኤል እንደተተኮሰባት ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

"ያልተጠበቀውና ኃላፊነት የጎደለው ጥቃት ሲሰነዘር፣ ላለፉት ስድስት ወራት የውሸት ፕሮፓጋንዳ በስፋት ተነዝቷል። አሁንም እየተነዛ ነው። ይህም ኤርትራን በሐሰት በመኮነን ትኩረቱን ከወንጀለኞች ለማሸሽ የሚደረግ ጥረት ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን "ሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳ" ያሉትንም በጥብቅ አውግዘዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተው ግጭት ውስጥ የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በጦርነቱ መሳተፉ በስፋት መገለጹ አይዘነጋም።

በዚህ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆነው የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ክልል ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን የሚጠቁሙ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ አሜሪካ ሠራዊቱ ክልሉን ክልልን ለቆ በአፋጣኝ እንዲወጣ በተደጋጋሚ ስታሳስብ ቆይታለች።

ሆኖም ግን ሠራዊቱ ከትግራይ ባለመውጣቱ፣ በክልሉ የሚካሄደው ጦርነት ባለመቆሙ፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ባለመሻሻሉ እና የግጭቱ ተሳታፊ ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ የተደረገው ጥረት ተቀባይነት ባለማግኘቱ አሜሪካ እርምጃ ወስዳለች።

በዚህም የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ባለሥልጣናት፣ በወታደራዊና የደኅንነት አባሎች፣ በአማራ ክልል ኃይሎች እንዲሁም በህወሓት አባላት ላይ የቪዛ እገዳ ጥላለች።

ኢትዮጵያ፤ አሜሪካ በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ እንደገባች በመግለጽ፤ አሜሪካ በዚሁ ከቀጠለች የሁለቱን አገራት ግንኙነት መለስ ብላ ለመመርመር እንደምትገደድ አስታውቃለች።

ወታደራዊ ግጭቱ ከስድስት ወራት በፊት ከተነሳ ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሲገደሉ፣ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

ከፍተኛ የሰብዓዊ ጥሰት መፈጸሙ እንዲሁም ሰብዓዊ እርዳታ በተገቢው መንገድ አለመድረሱም በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሪፖርት ተደርጓል።