በኤርትራ ምርጫ ተካሂዶ የማያውቀው ለምንድን ነው?

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

የኤርትራ ሕዝብ፤ በ1983 ዓ.ም ነጻነቱን ካገኘ በኋላ በዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የሚመራ መንግሥት ለመትከል ለ30 ዓመታት ቢጥርም፤ እስከ ዛሬ ሕገ መንግሥቱ ሥራ ላይ ሳይውል፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሳይካሄድ ቆይቷል። በቅርብ ዓመታት ውስጥ ይህ እንደሚሆን የሚታይ ፍንጭ የለም።

የአገሪቷ ፕሬዝደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ያልፈቀዱበት ምክንያት ምንድን ነው?

የኤርትራ የነጻነት ትግል

ሻዕቢያና የኤርትራ ነጻነት ትግል [ተሓኤ] "ቅኝ ግዛትን በማስወገድ ሕገ መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ ነጻ ኤርትራ" መገንባት የሚል አላማ ይዘው መታገላቸውን ኤርትራን በቅርበት የሚከታተሉ ምሁራን ይናገራሉ።

በሳሕል በተካሄደው ሁለተኛው ጉባኤ [እኤአ 1987] የወጣው አገራዊ ዴሞክራሲያዊ ፕሮግራም እንዲሁም በ1994 (እኤአ) በተካሄደው ሦስተኛው ጉባኤ የጸደቀው አገራዊ ቻርተር አላማው "ዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥታዊ መንግሥት መፍጠር" እንደነበረ የሕግ ሙሁር ዳዊት ፍስሃየ ይናገራሉ።

"ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መመስረት" በሚል ርዕስ በ1987 የተዘጋጀው ፕሮግራም "የትግሉ አላማ የሕዝብ ጥቅም የሚያስጠብቅ መንግሥት መመስረት ሆኖ፣ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ነጻ የሕዝብ ወኪል፣ ሕገ መንግሥት የሚያረቅ፣ አዲስ ውሎች የሚያጸድቅ፣ የዜጎች መብቶች የሚያስከብርና ሕዝብን የሚያገለግል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቆም" እንደነበረ ያስረዳል።

በ1994 የጸደቀው ቻርተር ደግሞ፣ አገራዊ የዴሞክራሲ ፕሮግራም ሃሳብን የሚያነሳ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ መጎስ ብርሃነ በበኩላቸው፤ "ሕግና ሥርዓት የሚያከብር፣ አንድነትና ሰላም የሚያስጠብቅ፣ አገራዊ አንድነት የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት" ያለመ ነበር ይላሉ።

በ1990 ፕሬዝደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የድርጅታቸው ሊቀመንበር በነበሩበት ወቅት፤ ሁሉም እንደየአቅሙ አገር በመገንባትና በአገሪቷ ላይ በሚገነባው ሥርዓት ተሳታፊነት እንዲኖረው፣ ሁሉንም የሚወክል ሥርዓት እንዲመጣ፣ የመድብለ ፓርቲ ሥርሥት እንዲገነባ፤ አንድ ፓርቲ የሚመራው የፖለቲካ ሥርዓት ግን መረጋጋትና ዋስትና እንደማይፈጥር መግለጻቸውን ያስታውሳሉ።

ታዲያ ሁኔታዎች በምን ምክንያት ተቀየሩ?

የኤርትራ ሕዝብ በ1993 በተካሄደው ሪፈረንደም 99.8 በመቶ ነጻነት መምረጡ ይታወሳል።

በግንቦት 19/1993 ደግሞ በአዋጅ 37/1993 ሕገመንግሥት እና የፕሬስ ሕግ የሚያረቅና የሚያጸድቅ እንዲሁም የፖለቲካ ድርጅቶች የሚመሩበት፣ አገራዊ ምርጫ የሚካሄድበት ሕግ የሚያዘጋጅ፣ አራት ዓመት የስልጣን እድሜ ያለው ጊዜያዊ መንግሥት እንደተቋቋመ የኤርትራውያን የሕግ ምሁራን ማኅበር አባል አቶ ኤልያስ ሃብተሥላሴ ይናገራሉ።

ይህ አዲስ መንግሥት ጊዜያዊ የኤርትራ መንግሥት በመባል እንደሚታወቅና ሕግ አውጪ፣ ሕግ ፈጻሚና፣ ሕግ ተርጓሚ አካላትን እንደሚያጠቃልል አዋጁ ያስረዳል።

ይህ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት የመገንባት ሂደት በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ግጭት እስኪስተጓጎል ድረስ ሕገ መንግሥት የሚያረቅ ኮሚሽን ደግሞ ግንቦት ወር 1997 ዓ.ም በኤርትራ ምክር ቤት ጸድቋል።

በ1996 ደግሞ የፕሬስ ሕግ ረቂቅ ተዘጋጅቶ የግል ጋዜጦች ተበራክተው ነበር።

"ሁሉም ኤርትራዊ በአገራዊ ጉዳዮች መሳተፍ አለበት" ሲሉ የነበሩት ፕሬዝደንት ኢሳይያስ ከነጻነት በኋላ በአገራዊ ጉዳዮች ለመሳተፍ ጥያቄ የሚያቀርቡ የተሓኤ አባላት "ከአሁን በኋላ የፖለቲካ ዥዋዥዌ አይፈቀድም" በማለት በግል እንጂ በፓርቲ ደረጃ መግባት እንደማይችሉ ከለከሉ።

"የኢሳያስ ባህሪ በሚገባ የሚገነዘብ ሰው ሕብረ ብሔራዊ ሥርዓት የመገንባት ፍላጎት አካባቢው ላይ የነበሩ ሰዎች ፍላጎት እንጂ የእሱ አይመስለኝም" ይላሉ አቶ ኤልያስ።

በርካታ የምክር ቤትና የመንግሥት አባላት በወጉ ማስቀረት ይቻል የነበረውን የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት መገምገም አለበት በማለት ከፕሬዝደንት ኢሳይያስ ጋር ከፍተኛ አለመግባባት ፈጥረው እንደነበረ ይታወሳል።

በወቅቱ በርካታ ዝግ ስብሰባዎች ሲካሄዱ ቆይተው በታኅሣሥ 2001 አገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ በመወሰን የምርጫ ሕግና የፖለቲካ ድርጅቶች የሚመለከት ሕግ የሚያረቁ ሁለት ቡድኖች ተመረጡ።

ሆኖም በወቅቱ የተዘጋጀው ሃሳብ ወደ ሕዝብ ቀርቦ ክርክር ሳይደረግበት በፕሬዝደንቱ ከተቋረጠ በኋላ ልዩነት በመበርታቱ በርካታ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ለእስር ተዳረጉ።

ከዚያ በኋላ የምርጫ ጉዳይ እንደ ሃሳብም ሳይነሳ እስከ ዛሬ ድረስ ተራዝሞ ይገኛል።

"እንደ እኔ አረዳድ" ይላሉ አቶ ኤልያስ፤ "በትጥቅ ትግል ወቅት ቫንጋርድ [የሁሉ የበላይ] ፓርቲ ሲመራ የነበረው ኢሳያስ ለማስመሰል ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲ እንመሰርታለን ሲል ነበር። በ1994 የተሰጣት ተልዕኮ ጨርሳ ፈርሳለች ያለን ድብቅ ፓርቲ አሁንም በሚስጥር የምትሰራ ይመስለኛል። ቫንጋርድ ፓርቲ ደግሞ ስልጣን ከሌሎች ጋር መጋራት ስለማይፈቅድ በዚህ ምክንያት ምርጫ ሳይካሄድ ቆይቷል እላለሁ።"

አቶ ዳዊት ፍስሃዬ ግን በ2001 በኤርትራ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት የመመስረት ሂደት የሚቃወም መፈንቅለ መንግሥት እንደተካሄደ ይናገራሉ።

"ፕሬዝደንት ኢሳያስ ምክር ቤት አፍርሶ ሕገ መንግሥታዊ መንግሥት እንዲገነባ የሚጠይቁ የቅርብ ሰዎችን ያለ ክስና ፍርድ አስሮና አጥፍቶ ፖሊሳዊ መንግሥት የመሰረተበት ምክንያት ምርጫ እንዳይካሄድ ነው።"

"ምርጫ ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያስችል ሂደት በመሆኑ ህግ ጥሶ በኃይል ሕገ ወጥ ተግባር የፈጸመ ሰው ተጠያቂ እንዲሆን አይፈልግም" በማለት አቶ ኢሳያስ እስከ መጨረሻው ምርጫ እንደማይፈቅዱ ይገልጻሉ።

ፕሬዝደንቱ ሃሳባቸው ለምን ቀየሩ?

የትጥቅ ትግል በተካሄደበት ወቅት "የኤርትራ ነጻነት ዘግይቶ የመጣው ስለሆነ የአፍሪካ መሪዎች የፈጸሙት አይነት ስህተት አትደግምም" የሚል አመለካከት እንደነበረ የሚናገሩት አቶ መጎስ ብርሃነ "ሕዝባችን ግን በሁሉም አይነት ጥፋት ስንከሳቸው ከነበሩት የአፍሪካ መሪዎች በታች መሆናችንን ተገንዝቦ ነበር" ይላል።

የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ግጭት እስከተከሰተበት ወቅትም ሁኔታዎች ከዛሬ ነገ ይስተካከላሉ በሚል ተስፋ ሲያደርግ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ሁሉም እንደታሰበው አልሆንም።

በ1988 አቶ ኢሳያስን የትጥቅ ትግሉ ማዕከል በነበረው ሳህል ውስጥ ለአራት ሰዓታት እንዳነጋገሯቸው የሚያስታውሱት አቶ ኤልያስ "ቻይና ውስጥ ምንድን ነው የተማራችሁት? ብዬ ጠይቄዋለሁ" ይላሉ።

"ብዙ ነገር እንደተማሩ ነገር ግን ቻይናውያን የማኦን አምልኮተ ሰብ [ፐርሰናል ካልት] መታገል እንደነበረባቸው ነገረኝ። ይሁን እንጂ ራሱ ሰብአዊ አምልኮ ፈጥሮ አገርን በአምባገነንነት ይዞ ይገኛል" ሲሉ ይኮንናሉ።

ፕሬዝደንት ኢሳይያስ አንድ በአሜሪካ የሚታተም ጋዜጣ "ስልጣንህ የመተው እቅድ አለህ ወይስ አፍሪካ አገራት መሪዎች እስክትሞት ትቆያለህ?" ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ "እኔ የኤርትራ ሕዝብ ሲጠይቀኝ ሳልዘገይ ስልጣኔን ለመተው ዝግጁ ነኝ። ምርጫው ሙሉ በሙሉ የሕዝብ ነው" ማለታቸውን ዘግቦ ነበር።

በተጨማሪም ፕሬዝደንት ኢሳይያስ 17ኛው የነጻነት በዓል በሚከበርበት ወቅት ከአልጀዚራ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኤርትራ መቼ ምርጫ ይካሄዳል የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

እርሳቸውም "አሜሪካ የምታካሂደው ምርጫ የሚመጣው ውጤትና እውነተኛ ምርጫ እስክናይ ለ30 ወይ ለ40 ዓመታት እንጠብቃለን . . ." ማለታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት በምርጫ ላይ ያላቸው አመለካከት ማሳያ ነው።

በተጨማሪም ፕሬዝደንት ኢሳያስ በ23ኛው የነጻነት በዓል ላይ ". . . ለሁኔታዎች የሚስማማ አዲስ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ እንጀምራለን" በሚል ተናግረው ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ በኤርትራ ምርጫ የሚባል እንደማይታሰብ ማረጋገጫ ነው የሚሉት አቶ ኤልያስ፤ "አቶ ኢሳያስ ስልጣን ላይ እያለ ምርጫ የማይ አይመስለኝም" ይላሉ።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ለሁለት አስርት ዓመታት ተፋጠው የነበሩት ኤርትራና ኢትዮጵያ ጉዟቸው ምን ይመስላል?