እነ አቶ ጃዋር ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤት መቅረብ እንደማይፈልጉ አስታወቁ

አቶ ጃዋር መሐመድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራር የሆኑት አቶ ጃዋር መሃመድና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ከ20 በላይ ተከሳሾች ጉዳያቸውን ፍርድ ቤት ቀርበው እንደማይከታተሉ በትናንትናው ዕለት ግንቦት 18፣ 2013 ዓ.ም አስታውቀዋል።

ተከሳሾቹ አቤቱታቸውን በአምስት ገፅ ደብዳቤ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ-ሽብር እና ህገ መንግሥታዊ ጉዳዮች እንዳቀረቡም ቢቢሲ ከጠበቆቻቸው አንዱ ከሆኑት አቶ ከድር ቡሎ ሰምቷል።

ትናነት በዋለው ችሎት ላይ በዋነኝነት ያነሱትም የፍርድ ቤት ውሳኔ በማይከበርበትና በተደጋጋሚ በህግ አስፈፃሚው አካል በሚጣስበት ሁኔታ የነሱ ችሎት መምጣት ትርጉም እንደሌለው ማስረዳታቸውንም አቶ ከድር ይናገራሉ።

ፍርድ ቤቱ ነፃ ቢለቃቸውም ህግ አስፈፃሚው አካል "ከህግ በላይ ሆኖ ስለማይለቀንና ፍርድ ቤቱም ውሳኔው በማይከበርበት ሁኔታ ችሎቱ የክብር ነው እንጂ መቀለጃ መሆን የለበትም" ብለዋል ይላሉ።

ለዚህም በርካታ ማጣቀሻዎች ማቅረባቸውን የሚናገሩት አቶ ከድር ከነዚህም መካከከል ፍርድ ቤት በነፃ ያሰናበታቸው እነ ኮሎኔል ገመቹ አያናና ሌሎች ግለሰቦች ፖሊስ ለመልቀቅ ፈቃደኛ አይደለም፤ እንዲሁም ያሉበት አይታወቅም።

የጂማ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮች እንዲሁ ፍርድ ቤቱ በነፃ ቢለቃቸውም ከቤተሰብም ሆነ ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት አልቻሉም፤ እስከዛሬ የት እንዳሉም አይታወቅም።

የኦነግ ስራ አስፈፃሚ የነበሩ አመራሮችም እንዲሁ ፍርድ ቤቱ ነፃ ቢያወጣቸውም ያለ ፍርድ ቤቱ እውቅና ታስረው እንዳሉና ያሉበት ቦታም ግልፅ እንዳልሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በባለፉት ሶስት ወራት ወደ አስር የሚጠጉ ግለሰቦች ከኦነግ ጋር በተገናኘ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በኦሮሚያ ፖሊስ ታስረው ይገኛሉ ብለዋል።

"ይህ የሚያሳየው የፍትህ መዛባትን ነው። የህግ አስፈፃሚው አካል ህግ አለማክበሩን ነው የሚያሳየው"ነው ማለታቸውን አቶ ከድር ያስረዳሉ።

አቶ ከድር እንደሚናገሩት ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለመከበር በተጨማሪ ግለሰቦች ያለ ፍርድ "በሚገደሉበት ሁኔታ"ን እንደ ምክንያትነት መጥቀሳቸውን አውስተዋል።

የትናንትና የፍርድ ቤት ውሎ የተጀመረው በህሊና ፀሎት ሲሆን እነ አቶ ጃዋር መሃመድና ተከሳሾቹ በዶምቢዶሎ ከተማ "በአደባባይ ላይ በቤተሰቦቹ ፊት" የተረሸነው አማኑኤል ወንድሙ እንዲሁም በትግራይ ጦርነት እየደረሰ ስላለው ግድያና ጥሰት የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እነ ጃዋር አከናውነዋል።

ቢቢሲ ከአማኑኤል ቤተሰቦች እንደተረዳው አማኑኤል ሲገደል በቦታው እንዳልነበሩና በኋላ ግን አስከሬኑን ወስደው እንዳሳዩዋቸው ገልፀዋል።

በትግራይ ካለው ጥሰት ጋር በተያያዘ የትግራይ ህዝብ ፆም (የረሃብ አድማ) እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው እነሱም የህዝቡ አካል ስለሆኑና ስለሚመለከታቸው ለሶስት ቀናት ከትግራይ ህዝብ ጋር የረሃብ አድማ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

በትግራይ ክልል ከገዳማት አባቶች በታወጀው መሰረት ከግንቦት 17-19 ድረስ ፆመ-ትግራይ በሚል የፆም፣ ፀሎትና የአርምሞ ቀናት እየተካሄደ ነው።

በትግራይ የተለያዩ ከተሞችም የንግድ ከተሞች ተዘግተውና ከእንቅስቃሴ ታቅበው እንደነበር ቢቢሲ ከነዋሪዎች የተረዳ ሲሆን በትግራይ ክልል ውስጥ በግጭቱ "የተገደሉ ዜጎችንና ካህናትን፣ የተደፈሩ ሴቶችን እንዲሁም የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትን" በማስታወስና ይሄም እንዲቆም ለማድረግ መሆኑ ተነግሯል።

በፀረ-ሽብር አዋጅ የተከሰሱት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ እነ ጃዋር መሃመድ በተጨማሪም ጠበቆቻቸው ጭምር ለእንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውንም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።

የጠበቆቻቸው መኪኖች እንደተሰበሩና አካላዊ ድብደባም ደርሶባቸዋል በማለት "ህግ በማይከበርበት ሁኔታ ችሎት መቅረብ የለብንም" ማለታቸውንም አቶ ከድር ያስረዳሉ።

ከዚህ ቀደምም ግንቦት 12፣2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት የፍርድ ቤት ቀጠሯቸው ከሁለት ዓመት በኋላ እንዲሆን ጥያቄ አቅርበው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ውድቅ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ከዚህ ቀደምም በነበረው ችሎትም ሆነ በአሁኑ የአቤቱታ ደብዳቤ ከምርጫውና አገር ከተረጋጋ በኋላ ወደ ፍርድ ቤቱ እንደሚመጡ ችሎቱን አስረድተዋል።