እስራኤል-ጋዛ፡ ኔታንያሁ የሃማስ ታጣቂዎች ለዓመታት ወደ ኋላ ተመልሰዋል አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል በጋዛ ያደረገችው የዘጠኝ ቀናት ድብደባ የሃማስ ታጣቂዎችን በበርካታ ዓመታት ወደ ኋላ የመለሰ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሁ ተናገሩ።
የእስራኤልና የፍልስጥኤም ግጭት አሁንም ጋብ አላለም።
በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት የፍልስጥኤም ታጣቂዎች ወደ ደቡባዊ እስራኤል በተኮሱት ሮኬት ሁለት የውጭ አገር የእርሻ ሠራተኞች ተገድለዋል።
እስራኤልም በጋዛ የምታደርገውን የአየር ድብደባ ቀጥላለች። በዌስት ባንክ በራማላህ አቅራቢያ በተደረገ ተቃውሞ ቢያንስ ሦስት ፍልስጥኤማዊያን በእስራኤል ፖሊሶች ተገድለዋል።
ግጭቱ እንዲቆም የተደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችም ያን ያህል ውጤት አላመጡም።
ፈረንሳይ ከግብጽ እና ጆርዳን ጋር በመተባበር ግጭቱን ለመፍታት የሚያስችል ረቂቅ ሃሳብ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አቅርባለች። አገራቱ የተኩስ አቁም ጥሪ አቅርበዋል።
ማክሰኞ ዕለት እስራኤል እርዳታ እንዲገባ ለመፍቀድ ወደ ጋዛ የሚወስደውን ድንበር የከፈተች ቢሆንም ከፍልስጤም ወታደሮች ሮኬቶች በመተኮሱ በድጋሜ ድንበሩ ተዘግቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ምንድን ነው ያሉት?
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታንያሁ "ጋዛን የሚያስተዳድረው የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኑ ሃማስ ያልተጠበቀ ዱብ ዳ አጋጥሞታል፤ ይህ ዘመቻም በእስራኤል ዜጎች ዘንድ መረጋጋት እስከሚመጣ ድረስ ይቀጥላል" ብለዋል።
እንደ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ እስካሁን ድረስ በጋዛ ቢያንስ 215 ሰዎች ተገድለዋል። ከእነዚህ መካከል 100 የሚሆኑት ሴቶችና ህጻናት ናቸው።
የጤና አገልግሎት ተቋም እንዳለው በእስራኤል ደግሞ ሁለት ህጻናትን ጨምሮ 12 ሰዎች ተገድለዋል።
ማክሰኞ ዕለት እስራኤል በጋዛ ከተገደሉት መካከል ቢያንስ 150 የሚሆኑት ታጣቂዎች እንደሆኑ አስታውቃለች። ይሁን እንጅ ሃማስ በወታደሮቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት በአሃዝ አልጠቀሰም።
ግጭቱ ከተከሰተ ጀምሮ እስራኤል ሁለቱ የፍልስጤም ታጣቂዎች ክንፍ 120 ሺህ የሚደርሱ ሮኬቶች በጋዛ እንደነበራቸው ግምቷን አስቀምጣለች።
ታጣቂዎቹ ከማክሰኞ ዕለት ከ9፡00 ሰዓት ጀምሮ 3 ሺህ 300 የሚሆኑ ሮኬቶችን እስራኤል ላይ ተኩሰዋል።
ከእነዚህ መካከል ከ450 እስከ 500 የሚደርሱት ከታለመው ሳይደርሱ በአጭር ቀርተው በጋዛ ጉዳት ማድረሳቸውን የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
በዌስት ባንክ የተፈጠረው ምንድን ነው?
በዌስት ባንክ እና በምስራቅ እየሩሳሌም ያሉ በርካታ ፍልስጥኤማዊያን እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ድብደባ በመቃወም አድማ መትተዋል። በእስራኤል የሚገኙና የእስራኤል አረቦች በብዛት በሚኖሩባቸው እንደ ሃይፋ ያሉ አካባቢዎች ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል።
የሕዝብ ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና በርካታ የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል።
በተለያዩ አካባቢዎችም ግጭቶች ነበሩ። በዌስት ባንክ ከተማ ራማላህ ሰላማዊ ባልሆነው ተቃውሞ ወቅት መተኮሳቸውን የእስራኤል ፖሊስ ተናግሯል።
በአካባቢው የነበሩ ሦስት ፍልስጥኤማውያን መገደላቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። በሄብሮን ወታደሮችን ለማጥቃት የሞከረ ሌላ ፍልስጤማዊ መገደሉንም የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
በእየሩሳሌም የደማስቆ መግቢያም ግጭቶች የነበሩ ሲሆን የእስራኤል ወታደሮች በርካቶችን አስረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድርጅት- ኦቻ በጋዛ 52 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መፈናቀላቸውንና ከእነዚህ መካከል 47 ሺህ የሚሆኑት ወደ ተባበሩት መንግሥታት ትምህርት ቤቶች መሸሻቸውን አስታውቋል።
ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች
በኒውዮርክ በቅርቡ በተደረገው ስብሰባ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ በድጋሚ ከስምምነት ላይ ሳይደርስ ቀርቷል።
ፈረንሳይ ያቀረበችው የመፍትሔ ሃሳብ የተዘጋጀው ከግብፁ መሪ አብደል ፈታህ አል ሲሲ እና ከጆርዳኑ ንጉስ አብዱላህ ሁለተኛ ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ወቅት መሆኑን አስታውቃለች።
አሜሪካ ከዚህ ቀደም የጸጥታው ምክር ቤት የተኩስ አቁም ጥሪ የሚያቀርብ የጋራ መግለጫ ለማውጣት የተደረጉ ጥረቶች ላይ ሳትስማማ ቀርታለች።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት እና ሌሎች ኃያላን ግጭቱ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። ግብጽ እስራኤልና ሃማስን ለማሸማገል እንደምትፈልግ ገልጻለች።
ይሁን እንጅ እስራኤል ሃማስን እና እስላማዊ ጅሃድን ለማጥፋት ጥቃት መፈፀሟን እንደምትቀጥል አስታውቃለች።
በተባበሩት መንግሥታት የፍልስጥኤም አምባሳደር ሪያድ ማንሱር የጸጥታው ምክር ቤት ወጥ አቋም አለማሳየቱን "አሳፋሪ" ብለውታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ የቱርኩ ፕሬዚደንትን ሬሲብ ታይፕ ኤርዶዋንን ስለ እስራኤል ተናግረዋል ባለችው 'ጸረ አይሁዳውያን' ንግግር ከሳለች።
ፕሬዚደንቱ በንግግራቸው በፍልስጥኤማውያን ላይ በምትፈጽመው ጥቃት እስራኤልን ከሰዋል። በቅርቡም "ይህ ተፈጥሯቸው ነው" በማለት "እስራኤል ገዳይ ናት" በማለት 'ጸረ አይሁዳውያን' ተደርጎ በስፋት የሚታይ ንግግር ተናግረዋል።
የአሜሪካ የፕሬዚደንት የታይፕ ኤርዶዋንን ንግግር በጥብቅ አውግዛለች። ፕሬዚደንት ኤርዶዋንና ሌሎች የቱርክ መሪዎች ተጨማሪ ግጭት ሊቀሰቅስ ከሚችል መሰል ንግግርም እንዲታቀቡ አሳስባለች።
ግጭቱን የቀሰቀሰው ምንድን ነው?
በእስራኤልና በሃማስ መካከል የተከሰተው ግጭት የተነሳው በፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን ፖሊስ መካከል በምሥራቅ እየሩሳሌም ቅዱስ ሥፍራ ለቀናት በተፈጠረ ግጭት ነው።
ሥፍራው በሙስሊሞችም ክብር የሚሰጠው ሲሆን ሃራም አል ሻሪፍ እያሉ ይጠሩታል።
አይሁዳውያን ደግሞ የተራራው ቤተ መቅደስ ይሉታል።
ሃማስ እስራኤል ፖሊሶቿን ከአካባቢውና በርካታ ሙስሊሞች ከሚኖሩበት የአረቦች ግዛት ሼክ ጃራህ እንድታነሳ ትፈልጋለች። ሼክ ጃራህ በርካታ የፍልስጥኤም ቤተሰቦች በአይሁድ ነዋሪዎች የተገደሉበት ነው።
ሃማስ ለዚህ ጥያቄው መልስ ሳያገኝ ቀረ። ከዚያም ሮኬት መተኮስ ጀመረ።
በእርግጥ የፍልስጤማውያን ቁጣ ለሳምንታት በእየሩሳሌም በነበረው ውጥረት ታምቆ የቆየ ነበር። ከሚያዝያ ወር አጋማሽ ጀምሮም ከፖሊሶች ጋር ግቶች ነበሩ።
ከዚያም እስራኤል እአአ1967 በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት፤ ምስራቅ እየሩሳሌምን በተቆጣጠረችበትና 'የእየሩሳሌም ቀን' ተብሎ በሚጠራው ዓመታዊ በዓል ላይ ሌላ ችግር ተቆሰቆሰ። ግጭቱ ለዓመታት የነበረ ይሁን እንጅ የሰሞኑ ግጭት መነሻ ግን ይኸው ነው።
ለሁለቱም ወገኖች ሃይማኖታዊና ብሔራዊ መሠረት ያላት የከተማዋ እጣ ፈንታም ለአስርት ዓመታት በዘለቀው የእስራኤልና ፍልስጤም ግጭት ላይ የወደቀ ነው።
እስራኤል እአአ በ1980 ምሥራቅ እየሩሳሌምና ጠቅላላ ከተማዋን እአአ በ2017 ዋና መዲናዋ አድርጋለች። ነገር ግን ይህ በአብዛኛው አገራት እውቅና አልተሰጠውም።
ፍልስጤም ደግሞ እመሰርተዋለሁ ብላ ላሰበችው ለራሷ አገር ዋና መዲናነት የምሥራቃዊ እየሩሳሌም ግማሹ ክፍል ይገባኛል ትላለች።












