ጋዛ፡ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር 'በጋዛ የሚደረገው ጥቃት ይቀጥላል' አሉ

ጋዛ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, ጋዛ

ዛሬ ንጋት ላይ እስራኤል ጋዛ ውስጥ በወሰደችው የአየር ድብደባ ሶስት ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጤና ባለሙያዎች ገልጸዋል።

የፍልስጤም ታጣቂዎች ወደ ቴል አቪቭ በርካታ ሮኬቶችን የተኮሱ ሲሆን በዚህም ምክንያት ነዋሪዎች ለቦምብ መከላከያ ተብለው ወደተሰሩ መጠለያዎች ሸሽተዋል።

የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሁለቱም ወገኖች ግጭቱን ለማርገብ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪውን እያቀረበ ነው።

ትናንት ቅዳሜ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ከፍልስጤም ፕሬዝደንት ማህሙድ አባስ ጋር በስልክ የተነጋገሩ ሲሆን እየተፈጠረ ያለው ነገር እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ደግሞ በጉዳዩ ላይ ዛሬ ስብሰባ ያካሂዳል።

ሰኞ እለት ወደለየለት ግጭት በገባው የሁለቱ አገራት አለመጋባባት እስካሁን ቢያንስ 148 ሰዎች ጋዛ ውስጥ መገደላቸውን የፍልስጤም ኃላፊዎች የገለጹ ሲሆን እስራኤል ደግሞ ሁለት ህጻናትን ጨምሮ 10 ሰዎች ሞተዋል ብላለች።

እስራኤል በጋዛ ከሞቱት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ታጣቂዎች ናቸው ብትልም የፍልስጤም ባለስልጣናት ግን ከሟቾች መካከል 41 ህጻናት እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ቅዳሜ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በቴሌቪዥን መስኮት ባስተላለፉት መልዕክት የአየር ጥቃቶቹን አስፈላጊ እስከሆኑ ድረስ እንደሚቀጥሉበት ገልጸዋል። ንሑሀን ዜጎች ጉዳት እንዳይደርስባቸውም የቻሉትን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነም አስረድተዋል።

‘’አሁን ለተፈጠረው ፍጥጫ ጥፋተኞቹ እኛ አይደለንም፤ እኛ ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ያሉት ናቸው’’ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ባለፉት አምስት ቀናት በግጭት እየተናጠ ያለው ይህ ግዛት ካለፉት አመታት በቀጠናው ከተከሰተው የከፋ ነው ተብሏል።

በምስራቅ ኢየሩሳሌም በእስራኤልና በፍልስጤማውያን መካከል ለሳምንታት የዘለቀው ውጥረት ወደ ግጭት ያመራው በያዝነው ሳምነት መጀመሪያ ሰኞ እለት ነው።

በእስልምናና በአይሁድ እምነት ተከታዮች ዘንድ ቅድስት ተብላ የምትጠራው ስፍራ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ መጋጋል ተፈጥሮ ነበር።

ጋዛን የሚያስተዳድረው ታጣቂው ሃማስ እስራኤል ከቅድስቲቷ ስፍራ ለቃ እንድትወጣ ካስጠነቀቀ በኋላ ሮኬቶ ማስወንጨፉ ተገልጿል። እስራኤልም በምላሹ የአየር ጥቃቶችን ፈፅማለች።

አሜሪካም ብትሆን በእስራኤልና ፍልስጤም መካከል ያለው ግጭት ከፍ ወዳለ ጦርነት ሊያመራ ይችላል በተባለበት ወቅት ግጭቶቹን ለማርገብ ለሚደረገው ውይይት ልዑኳን ልካለች።

ሃዲ አሚር ከእስራኤል፣ ከፍልስጤምና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተውጣጡ ኃላፊዎች ጋር በሚደረገው ውይይት ይሳተፋሉ።

ውይይቱም የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ተስፋ ተጥሎበታል።

በእስራኤል የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እንዳስታወቀው የልዑኩ ጉዞ "ዘለቄታዊ ሰላም እንዲመጣ የሚሰሩ ስራዎችን ለማገዝ" እንደሆነ ቢያትትም የእስራኤልና የፍልስጤም ባለስልጣናት ተኩስ እንዲያቆሙ የቀረበላቸው ተማፅኖ ፍሬ አላፈራም።

ትናንት ቅዳሜ ላይ ደግሞ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ድብደባ አልጀዚራ እና አሶሼትድ ፕረስ እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶችና ነዋሪዎች ይጠቀሙበት የነበረ ህንጻ ሙሉ በሙሉ ፈርሷል።

የእስራኤል መከላከያ ወዲያው ባወጣው መግለጫ ህንጻውን ጋዛን የሚያስተዳድረው የሀማስ ቡድን ታጣቂዎች ሲጠቀሙበት ነበር ብሏል። የህንጻው ባለቤት ግን ከዚህ ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሀን የሚጠቀሙበት ህንጻ ላይ በደረሰው ጥቃት በጣም መደንገጣቸውን አስታውቀዋል።

‘’ዋና ጸሀፊው በሁለቱም ወገኖች በከኩል ንጹሀን ዜጎች እና የመገናኛ ብዙሀን ላይ የሚደርሱ ትቃቶች በርካታ ዓለማቀፍ ሕጎችን የሚጥሱና በቶሎ መቆም ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው’’ ብለዋል ሲል የዋና ጸሃፊው ቃል አቀባይ አስታውቋል።