ኮቪድ-19፡ ዌስት ቨርጂኒያ ወጣቶች ክትባት እንዲከተቡ ለማበረታታት 100 ዶላር ልታድል ነው

የምትከተብ ወጣት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የግዛቷ ገዥ ለወጣቶቹ የሚሰጠው የማበረታቻ ገንዘብ መቶ ዶላር እንደሆነም አስታውቀዋል።

የአሜሪካ ግዛት ዌስት ቨርጂኒያ ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 35 ለሚሆኑ ወጣቶች ክትባት ለመውሰድ እንዲነሳሱ ማበረታቻ ይኾን ዘንድ የኪስ ገንዘብ ልትሰጥ ነው።

የግዛቷ ገዥ ጂም ጀስቲስ ሰኞ እንደተናገሩት "ልጆቻችን አሁን ላይ ይህን ክትባት ወስደው ወረርሽኙን ማቆም ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ላይረዱት ይችላሉ" ሲሉ የኪስ ገንዘብ ዕደላው ያስፈለገበትን ምክንያት አስረድተዋል።

የግዛቷ ገዥ ለወጣቶቹ የሚሰጠው የማበረታቻ ገንዘብ መቶ ዶላር እንደሆነም አስታውቀዋል።

ዌስት ቨርጂኒያ ነዋሪዎች ክትባት በመውሰድ ረገድ ከአሜሪካ ግዛቶች ፈጣን ከሚባሉት አንዷ ብትሆንም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ግን ነዋሪዎቿ ክትባቱን ለመውሰድ ዳተኛ ሆነው ታይተዋል።

በበርካታ የአሜሪካ ግዛቶች ወጣቶች ክትባት ለመውሰድ አሻፈረኝ ይሉ ይሆን የሚል ስጋት አሁንም እንዳለ ነው።

የክትባት ጉርሻ መቶ ዶላሩ የሚሰጠው ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 35 ለሆኑ ወጣቶች ሲሆን ክትባት መውሰዳቸውን ተከትሎ ወዲያውኑ ተከፋይ ነው። ቆየት ብለው መውሰድ ከፈለጉም መቶ ዶላሩ ከነወለዱ ይከፈላቸዋል።

ቀደም ብለው ክትባት የወሰዱ ወጣቶችም ቢሆን ገንዘቡን ከፈለጉ ይኸው ተፈጻሚ ይኾናል።

ዌስት ቨርጂኒያ ከአሜሪካ 50 ግዛቶች በቫይረሱ ሥርጭት ረገድ 16ኛዋ ግዛት እንደሆነች ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

ከአንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ክትባት ይወስዳሉ ተብለው ከሚጠበቁ ነዋሪዎቿ 52 ከመቶ የሚሆኑት ይህንኑ ያደረጉ ሲሆን 40 ከመቶ ግን ሊያንገራግሩ ይችላሉ የሚል ፍርሃት አለ።

የግዛቲቱ ገዥ ጀስቲስ "ለማድረግ ያሰብኩት ወጣቶቹን ማነቃቃት ነው፣ ክትባቱን እንዲወስዱ ሊያበረታታ የሚችል ነገር ካሰብን በኋላ ነው ይህን የኪስ ገንዘብ ሐሳብ ያመጣነው" ብለዋል።

የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከትልልቅ ሰዎች ይልቅ ወጣቶች ክትባት በመውሰዱ ረገድ ዳተኛ ሊሆኑ ይችላሉ።

በአሜሪካ 25 ከመቶ የሚሆኑ ወጣቶች 'ክትባቱን ትወስዳላችሁ ወይ?' በሚል ተጠይቀው "ነገሮችን አጢነን እንጂ አሁን መውሰድ አንፈልግም" የሚል ምላሽ እንደሰጡ ጥናቶች ያሳያሉ።

ተመሳሳይ አሉታዊ ምላሽ የሰጡ ዕድሜያቸው ከ65 በላይ የሆኑት ግን ከመቶ ሰባት እጅ እንኳን አይሞሉም።

በአሜሪካ በአሁን ሰዓት ዕድሜው ከ16 ዓመት በላይ የሆነ ማንኛውም ዜጋ ክትባት ለመውሰድ ብቁ ነው።

እስከአሁን አሜሪካ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ዜጎቿን ቢያንስ አንድ ጠብታ ክትባት እንዲያገኙ አድርጋለች። የአፍ-ወ-አፍንጫ ጭንብል ማጥለቅ ግዴታም በቅርብ ጊዜ ውስጥ እየላላ ሊመጣ ይችላል እየተባለ ነው።