አሜሪካ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ጣለች

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካ መንግሥት ሩሲያ ባደረሰችው የሳይበር ጥቃትና ሌሎች "ጠብ አጫሪ" ድርጊቶች ምላሽ የሚሆን ማዕቀብ እንደጣለ አስታውቋል።

ማዕቀቡ መጠነ ሰፊ እንደሆነ የገለፀው ዋይት ሃውስ ከእርምጃዎቹም መካከል የሩሲያ ተቋማትና ባለስልጣናት ኢላማ ናቸው ተብሏል።

አላማውም "የሩሲያ በጥላቻ የተሞላ ተግባራትን" መግታት ነው ብሏል ዋይት ሃውስ በመግለጫው።

መግለጫው አክሎም በባለፈው አመት በነበረው የሶላር ዊንድ የሳይበር ጠለፋ ጀርባ የሩሲያ ደህንነት አለበት ከማለት በተጨማሪም በባለፈው የአሜሪካ ምርጫ ሞስኮ ጣልቃ ገብታለች ብሏል።

ሩሲያ በበኩሏ ይሄንን አልፈፀምኩም ብላ የተናገረች ሲሆን ለዚህ ማዕቀብም አፀፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ አስታውቃለች።

ትናንትና ሃሙስ የታወጀው ማዕቀብ ዝርዝር እርምጃዎችን የያዘ ሲሆን የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፍፁማዊ ትእዛዝ ፊርማ አርፎበታል።

በከፍተኛ ሁኔታ ቅራኔ ውስጥ የገቡት ሁለቱ አገራት አሁን ደግሞ ወደባላንጣነት በሚባል ሁኔታ እየተሸጋገሩ ነው።

ባለፈው ወር አሜሪካ ሰባት የሩሲያ ባለስልጣናትንና በርካታ የሩሲያ መንግሥት ተቋማትን መንግሥትን በሚተቸው አሌክሴ ናቫልሊ መመረዝ ምክንያት ኢላማ አድርጋቸው ነበር።

ሩሲያ በበኩሏ በአሌክሴ መመረዝ እጄ ከደሙ ንፁህ ነው ትላለች።

ጆ ባይደንና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማክሰኞ እለት ባደረጉት የስልክ ልውውጥ ባይደን አገራቸው ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር "ቆፍጠን ያለ እርምጃ ትወስዳለች" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ ሁለቱ አገራት አብረው ሊሰሩባቸው የሚችሉ ሁኔታዎችን እንዲመቻችም ለሩሲያ አቻቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን በሩሲያ ላይ የተደረገው የማዕቀብ ውሳኔ "ተመጣጣኝ ነው" ብለውታል።

"ከፑቲን ጋር ባደረግረው ንግግርም የአሜሪካን ውሳኔ አሳውቄያቸዋለሁ። ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ወደፊት መግፋት እንችል ነበር ነገር ግን እሱን አልመረጥኩም" በማለት ፕሬዚዳንት ባይደን ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።

አክለውም "አሜሪካ ማለቂያ የሌለው ውጥረትና ግጭት ውስጥ ከሩሲያ ጋር መግባት አትፈልግም" ብለዋል።