የቴፕ ካሴትን የፈለሰፉት ግለሰብ በ94 ዓመታቸው አረፉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የቴፕ ካሴትን የፈለሰፉት የሆላንዱ መሃንዲስ ሉዎ ኦቴንስ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የቴፕ ካሴቶች በ1960ዎቹ መፈጠራቸውን ተከትሎ እስካሁን ባለው መረጃ ከ100 ቢሊዮን በላይ ካሴቶች በአለም ላይ ተሽጠዋል።
የሉዎ ኦቴንስ ፈጠራ ሰዎች ሙዚቃ የሚሰሙበትን መንገድ አንድ እርምጃ አራምዶታል ተብሏል።
መሃንዲሱ በትውልድ ቦታቸው ዱይዜል በባለፈው ሳምንት መጨረሻ እንዳረፉ ቤተሰቦቻቸው አስታውቀዋል።
በአውሮፓውያኑ 1960 የፊሊፒስ ኩባንያ የምርቶች ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት ሉዎ ኦቴንስ በዚያኑ ወቅትም ነበር ከስራ አጋሮቻቸው ጋር የቴፕ ካሴትን የፈጠሩት ተብሏል።
በአውሮፓውያኑ 1963 በርሊን በተዘጋጀው የሬድዮ ኤሌክትሮኒክስ አውደ ርዕይ ላይ ካሴቶቹ መቅረባቸውን ተከትሎ በአለም ላይ ዝናቸው ናኝቷል።
መሃንዲሱ ካሴቶቹን በፈጣሪነት ማስመዝገብ ከቻሉም በኋላ ከፊሊፕስና ሶኒ ጋር ስምምነቶች ላይ ደርሰው ነበር።
የሳቸውን ሞዴል መሰረት በማድረግም የጃፓን ኩባንያዎች በተመሳሳይ የቴፕ ካሴቶችን ያመርቱ ነበር ተብሏል።
የቴፕ ካሴቶቹ የተፈጠሩበት አምሳኛ አመት መታሰቢያ በሚከበርበትም ወቅት ከመጀመሪያው ጀምሮ " አስደናቂ ነበሩ" በማለት ለኒውዮርክ ታይምስ ተናግረዋል።
ከቴፕ ካሴቶቹም በኋላ መሃንዲሱ በሲዲ (ኮምፖክት ዲስክ) ስራ ላይ ተሳትፈዋል። በአለም ላይም ከ200 ቢሊዮን በላይ ሲዲዎች መሸጣቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
ከሙያቸውና ከፈጠራቸው ጋር በተያያዘ የሚፀፀቱበት ነገር እንዳለ በአንድ ወቅት የተጠየቁት ሉዎ ኦቴንስ የቴፕ ካሴት ማጫወቻ የሆነው ወክማን በፊሊፕስ ሳይሆን በሶኒ መፈጠሩ እንደሚፀፅታቸው ተናግረዋል።
ከገበያው ገሸሽ ብለው የነበሩት የቴፕ ካሴቶች በቅርብ አመታት ውስጥ እንደ አዲስ እውቅናን አግኝተዋል። ሌዲ ጋጋና ዘ ኪለርስ የመሳሰሉ አርቲስቶችም ሙዚቃቸውን በካሴቶች አሳትመው አውጥተዋል።
የሙዚቃ ሽያጮችን በበላይነት የሚከታተለው የዩኬ ኩባንያ የባለፈው አመት የካሴት ሽያጮች ከዚያ ቀደም ከነበረው አመት ጋር ሲወዳደር በ103 በመቶ መጨመሩን ያሳያል ይላል።
የአሜሪካው ኒልሰን የሙዚቃ ኩባንያ በበኩሉ በአሜሪካ የካሴቶች ሽያጭ በ23 በመቶ ጭማሬ ማሳያቸውን አስታውቋል።













