ትግራይ ፡ መንግሥት በትግራይ ለ1.8 ሚሊዮን ሰዎች የሰብአዊ ድጋፍ መድረሱን ገለጸ

ወደ ሱዳን ከተሰደዱት ሰዎች መካከል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በትግራይ ክልል ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችና የሕክም አቅርቦቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ለ1.8 ሚሊዮን ሰዎች መድረሱን የሠላም ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች እየቀረበ ያለውን እርዳታ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ ከተጠቀሱት ሰዎች በተጨማሪ በክልሉ 2.5 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አመልክቷል።

እየቀረበ ያለው የሰብአዊ ድጋፍ ስርጭት የሚከናወነው ከአክሱም፣ ከአዲግራት፣ ከአላማጣ፣ ከመቀለ ዙሪያ፣ ከሽሬ እና መቀለ ከተማ ከሚገኙ የማሰራጫ ጣቢያዎች መሆኑን አመልክቶ፤ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ለሚቀርበው ድጋፍና አገልግሎት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ተብሏል።

የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱ በአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል የሚኒስትሮች ኮሚቴ መሪነት አፋጣኝ ፍላጎቶችን ለማሟላት ከሚንስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ከክልል ቢሮዎች፣ ከተባበሩት መንግሥታት ተቋማትና ከዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጣ የቴክኒክ ቡድኖችን ያካተተ የአስቸኳይ ጊዜ ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ ማዕከል በመቀለ ከተማ መቋቋሙንም አመልክቷል።

የሠላም ሚኒስቴር ጨምሮም አሁን እየቀረቡ ካሉ የሰብአዊ ድጋፎች በተጫማሪ ያሉ ፍላጎቶችን ለመለየት በተለያዩ የአስተዳደር ደረጃዎች የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበር ሥርዓት ተደራጅቶ እየሰራ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ ለተጠቃሚዎች የድጋፍ ሽፋንን ለማሳደግ እንዲሁም በፍጥነት አቅርቦትን ለማዳረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ከልማትና ከሰብዓዊ አጋሮች ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ ይገኛል ብሏል።

በክልሉ የተሰማራው የአገር የመከላከያ ሠራዊትም የሰዎችና የሰብአዊ አቅርቦቶች እንቅስቃሴን ደኅንነት በመጠበቅና በማመቻቸት እየተከናወነ ያለውን ሥራ በከፍተኛ ደረጃ በመደገፍ ላይ ይገኛል ተብሏል።

በሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱ ሂደት ውስጥ መንግሥታዊ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ዓለም አቀፍና በአገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አማካይነት እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።

ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ጉዳዮች ተቋማት በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች በአፋጣኝ ዕርዳታ ማቅረብ ካልተቻለ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

በመንግሥት የሚመራው የትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል በክልሉ የተካሄደውን ግጭት ተከትሎ የሚያስፈልጉ ነገሮችን በተመለከተ ጥናት እያካሄደ እንደነበር ገልጾ ነበር።

በተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰውና የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል እንደሚለው በትግራይ ክልል 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል።

ታኅሣስ 30/2013 ዓ.ም በትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል አማካይነት በተካሄደው ስብሰባ ላይ በአንድ ተሳታፊ አማካይነት የተነሱ ነጥቦች የሰፈሩበትና ሾልኮ የወጣው ማስታወሻ እንደሚያሳየው፤ የማዕከላዊ ትግራይ ክፍል የጊዜያዊ አስተዳደሪ አንድ ባለሥልጣን እንዳሉት "በስፍራው ያለው ሁኔታ በጣም የከፋ ነው" ሲሉ ገልጸውት ነበር።

ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልልና አዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ደኅንነትና ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንና የሰብአዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ማሳሰቡ ይታወሳል።

ኮሚሽነሩ ጨምረውም የችግሩ ተጎጂዎች በቂ ያልሆነ ወይም ምንም እርዳታ እንዳላገኙ ገልጸው "በአካባቢዎቹና በሠላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ከሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛና አፋጣኝ ርብርብ የሚጠይቅ ነው" በማለት ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው አሁን ድረስ ወደ ተወሰኑ የትግራይ አካባቢዎች ለመግባት ውስንነት ቢኖርም የተወሰነ የዕርዳታ ድጋፍ ግን እየገባ ነው።

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በሚገኘው ሠራዊቱ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት ከተሰነዘረበት በኋላ ነበር ወታደራዊ ዘመቻ የከፈተው።

ይህንንም ተከትሎ ለሦስት ሳምንታት ያህል የተካሄደውን ውጊያ በመሸሽ ከ50 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን መሰደዳቸው የተነገረ ሲሆን፣ በርካቶች ደግሞ በአገር ውስጥ ሆነው የመሠረታዊ አቅርቦቶች ችግር እንደገጠማቸው የዕርዳታ ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።

በክልሉ በአብዛኛው ቦታዎች ለረጅም ጊዜ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም አገልግሎቶች ተቋርጠው በመቆየታቸው ምክንያት ትክክለኛ አሃዝና መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

የሠላም ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥትና የሰብአዊ ድጋፍ አጋሮች ኅዳር 20/2013 ዓ.ም በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ዕርዳታ የማቅረቡን ሥራ በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን አመልክቷል።