አሜሪካ፡ ከአፈጉባኤዋ ጽህፈት ቤት መረጃ ሰርቃለች የተባለችው የትራምፕ ደጋፊ ተያዘች

ራይሊ ጁን ዊሊያምስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ራይሊ ጁን ዊሊያምስ

በአሜሪካ ካፒቶል አመፅ ወቅት ከዴሞክራቷ አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ጽህፈት ቤት ላፕቶፕ ወይም ሃርድ ድራይቭ ሰርቃለች የተባለች የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ በቁጥጥር ስር ዋለች።

የ22 ዓመቷ ራይሊ ጁን ዊሊያምስ በኃይልና በሕገወጥ መንገድ ወደ ሕንፃው በመግባት እንዲሁም በሥርዓት አልበኝነት ተከሳ ፔንሲልቬንያ ውስጥ ተይዛለች።

አንድ የቀድሞ የፍቅር አጋሯ፣ ራይሊ መረጃውን ለሩሲያ የስለላ ተቋም ለመሸጥ አስባ እንደነበር ተናግሯል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የትራምፕ ደጋፊዎች ካፒቶል ሒልን የወረሩ ሲሆን፣ በተፈጠረው ግርግርም የአምስት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ይታወሳል።

የጆ ባይደን የምርጫ ውጤትን ለማረጋገጥ ተሰብስበው የነበሩትን ሕግ አውጪዎች የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች ወደ ካፒቶል ህንፃ ገብተው ከረበሹ በኋላ ራይሊን ጨምሮ ከ200 በላይ ሰዎች ጉዳያቸው እየታየ ነው።

ራይሊ ሰኞ ዕለት በማዕከላዊ ፔንሲልቬንያ ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሏን የፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

ራይሊ በፈቃዷ ለባለስልጣናት እጇን መስጠቷን ምንጮች ለሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

የክስ ዝርዝሯ "ያለ ፈቃድ እያወቁ ወደ ተከለከለ ሕጋዊ ቦታ መግባት ወይም በካፒቶል ግቢ ውስጥ ሥነ ምግባር በጎደለው ድርጊት ላይ መሠማራትን" ያካትታል።

ክሱ ከመረጃ ስርቆት ጋር የተያያዘ ጉዳይን አይጠቅስም። ኤፍቢአይ ጉዳዩን እየመረመረ መሆኑም ተዘግቧል።

ራይሊ በቴሌቪዥን መስኮቶች ወደ ካፒቶል ሒል ህንጻ ዘልቀው የገቡ ሰዎችን ስትመራ እንደታየች ተነግሯል።

የኤፍቢአይ ወኪል የግለሰቧ የቀድሞ የፍቅር አጋር፣ ራይሊ የፔሎሲን ላፕቶፕ ወይም ሃርድ ድራይቭ [የመረጃ ማከማቻ] ለመውሰድ አስባ እንደነበር ጥቆማ እንደተሰጠ ተገልጿል።

ምስክሩ፣ ራይሊ "ኮምፒውተሩን ሩሲያ ለሚገኘው አንድ ጓደኛዋ ለመላክ እንዳሰበች ገልጾ፣ ከዚያ ለሩሲያ የውጭ የስለላ አገልግሎት (SVR) ለመሸጥ አቅዳ ነበር" ብሏል።

መረጃውን የማስተላለፉ ፍላጎት "ባልታወቁ ምክንያቶች አለመሳካቱንና ራይሊ አሁንም ኮምፒውተሩ በእጇ አለ አልያም አጥፍታዋለች" ሲል ምስከሩ መናገሩ ተገልጿል።

የፔሎሲ ሠራተኞች ምክትል ኃላፊ ድሪው ሃሚል፣ ጥቃቱ ከተፈፀመ ከሁለት ቀናት በኋላ በትዊተር ገፃቸው ላይ አንድ ላፕቶፕ ከአፈጉባኤዋ ቢሮ እንደተሰረቀ ገልጸው ነበር።

ራይሊ የምትባል አንዲት ሴት በቴሌቪዥን መስኮት የታየች ሲሆን ሕዝቡ ወደ ፔሎሲ ቢሮ በሚወስደው ደረጃ እንዲሄድ ስትመራ ተሰምታለች።

ከጥቂት ቀናት በኋላ አይቲቪ ከራይሊ እናት ጋር በሃሪስበርግ ፔንሲልቬንያ በሚገኘው ቤታቸው በሠራው ቃለመጠይቅ በቴሌቪዥን የታየችው ልጃቸው መሆኗን አረጋግጠዋል። ልጃቸው ወዴት እንደምትሄድ ሳትናገር ከቤት እንደወጣች ተናግረዋል።

ባልተረጋገጠ መረጃ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ድምጽ ተሰርቋል ብለው የሚያምኑ የቀኝ ዘመም ቡድኖች እና ሌሎችም ተጨማሪ ጥቃቶች እንዳይሰነዝሩ በመስጋት ረቡዕ ዕለት ከሚካሄደው የጆ ባይደን በዓለ ሲመት በፊት የደኅንነቱ እርምጃው ተጠናክሯል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ከቀሰቀሱት ግርግር ጋር በተያያዘ አራት ሰዎች ሞቱ