የካፒቶሉን ነውጥ ተከትሎ ኩባንያዎች ፖለቲካዊ የገንዘብ ልገሳቸውን ሰረዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በባለፈው ሳምንት በዋሽንግተን የተነሳውን ነውጥ ተከትሎ በአሜሪካ ምክር ቤት ያሉ ሪፐብሊካኖች ከአገሪቱ ኩባንያዎች ዘንድ ከፍተኛ ውግዘትን አትርፈዋል።
በርካታ ቁጥር ያላቸው የአሜሪካ ኩባንያዎች ለምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያበረክቱት የነበረውንም ልገሳ እንሰርዛለን ብለዋል።
በተለይም ጆ ባይደን እንዳይመረጡ ለማድረግ ልገሳ ያበረከቱት ኩባንያዎች ለምርጫ ቅስቀሳ ገንዘብ ከአሁን በኋላ አንለግስም ብለዋል።
የፖለቲካ ልገሳዎችን ከሰረዙት ኩባንያዎች መካከል በሆቴል ዘርፉ ስመ ጥር የሆነው ማሪዮት፣ ሲቲ ባንክ እንዲሁም ስመ ገናናው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጉግል ይገኙበታል።
የትራምፕ ደጋፊዎች ካፒቶልን ሰብረው መግባታቸውን ተከትሎ ሌሎች ኩባንያዎችም እንዲሁ ስትራቴጂያቸውን እያጤኑት እንደሆነ ተናግረዋል።
ተመራጩን ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን የፕሬዚዳንትነት ማረጋገጫ ለማስቆም ባለመው በዚህ ነውጥ የአምስት ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል።
በርካታ ቁጥር ያላቸው የአሜሪካ ኩባንያዎች ለሁለቱም ፓርቲ አባላት የሚሆን ልገሳ ማድረግ የተለመደ ነው።
ሆኖም በቅርቡ የደረሰውን ነውጥ ተከትሎ ከህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ውግዘት በመፈጠሩ እነዚህም ኩባንያዎች ልገሳቸውን እንደገና እንዲያጤኑት በር ከፍቶላቸዋል።
በአካውንቲንጉ ዘርፍ የታወቀው ዴሎይቴ፣ የቴሌኮሙ ኤቲ ኤንድ ቲ እንዲሁም የክሬዲት ካርድ ኩባንያዎቹ አሜሪካን ኤክስፕረስና ማስተር ካርድ ማንኛውንም አይነት ልገሳ ለጊዜው አንሰጥም ብለዋል።
"ፖሊሲያችን እንዲህ አይነት የጥላቻ ቡድኖችን አባልነት አይቀበልም፤ ስለዚህ እነዚህን ግለሰቦች አባል መሆናቸውን ካወቅን እናግዳቸዋለን" በማለትም በአለም አቀፍ ዘንድ ግለሰቦች ቤቶቻቸውን እንዲያከራዩ የሚያስችለው ኤይርቢኤንቢ የተባለው ኩባንያ አስታውቋል።
ኩባንያው የ ጆ ባይደንን የመጪው ፕሬዚዳንትነት ማረጋገጫን የተቃወሙትን በሙሉ ምንም አይነት ድጋፍ አልሰጥም በማለትም አስታውቋል።
የሰላምታ ካርዶች አምራች ሆልማርክ በበኩሉ የጆ ባይደንን ፕሬዚዳንትንት ተቃውመዋል ያላቸውን ሁለት የሪፐብሊካን ሴናተሮች የሰጣቸውን ልገሳ እንዲመልሱ ጠይቋል። ኩባንያው በካንሰስ ዋነኛ የሚባልም ቀጣሪ ነው።
የኬሚካል ንጥረ ነገሮች አምራቹ ዶውም ከሌሎች ኩባንያዎች በተለየ መልኩ ለሪፐብሪካኖች የምክር ቤት አባላት በስልጣን ባሉበት አመታት ሁሉ ማንኛውም የገንዘብ ልገሳ አላድርግም ብሏል።
የአንዳንዶቹ ኩባንያዎች የገንዘብ እገዳ እስከተወሰነ ጊዜ የሚቆይ ሲሆን ከነዚህም መካከከል ጄኔራል ኤሌክትሪክ እስከ አውሮፓውያኑ 2022 ይዘልቃል ብሏል።












