ዶናልድ ትራምፕ፡ ኩባ ዳግም ሽብርን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ ገባች

የፎቶው ባለመብት, EPA
አሜሪካ ኩባን ሽብርን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ መልሳ አስቀመጠች።
አሜሪካ ይህን ያደረገችው ኮሚኒስቷ አገር ኩባ ቬንዙዌላን ትደግፋለች በሚል ነው።
የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ይህንን ያስታወቀው ዋይት ሃውስን ለቀው ለመውጣት የቀናት እድሜ ሲቀረው ነው።
በአውሮፓዊያኑ ጥር 20 ቢሮውን የሚረከቡት ተመራጩ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ከዚህ ቀደም የአሜሪካና የኩባን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።
ኩባ ውሳኔውን 'ፖለቲካዊ ጥቅመኝነት' ነው ስትል ተቃውማዋለች።
ጆ ባይደን በረዥም ጊዜ ባላጋራዎች መካከል የጠበቀ ግንኙነት እንዲፈጠር እንደሚፈልጉ ገልፀው፤ የፕሬዚደንት ትራምፕ ውሳኔ ግን ግንኙነቶች በፍጥነት እንዳይስተካከሉ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ተናግረው ነበር።
ተንታኞች እንደሚሉት ኩባ በዚህ ዝርዝር ውስጥ እንዴት እንደተካተተች ለማወቅ ወራቶችን ሊወስድ የሚችል መደበኛ ግምገማ ማድረግ እንደሚጠይቅ ገልፀዋል።
በካሪቢያን ባህር የምትገኘው ደሴታማዋ አገር ኩባ፤ ከዚህ ዝርዝር ውስጥ የወጣችው በፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ በ2015 ነበር።
አሁን እዚህ ውሳኔ ላይ ለምን እንደተደረሰ ሲገለፅ፤ ባለሥልጣናት ኩባ በአሜሪካ እውቅና የሌለውን የቬንዙዌላ መሪ ኒኮላስ ማዱሮን ትደግፋለች የሚል ምክንያት ያስቀምጣሉ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ሰኞ ዕለት "በዚህ ውሳኔ የኩባን መንግሥት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተጠያቂ እናደርጋለን፤ ግልፅ መልዕክትም እናስተላልፋለን። የካስትሮ አስተዳደር ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን መደገፍ እና የአሜሪካን የፍትህ ሥርዓት ማፍረስ ማቆም አለበት" ብለዋል።
የኩባ ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ብሩኖ ሮድሪጊዝ በምላሹ በትዊተር ገጻቸው "ኩባ በአሜሪካ ሽብርን የምትደግፍ አገር ተደርጋ በአንድ ወገን ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እና ግብዝነት በተሞላበት መስፈርት መቀመጧን እናወግዛለን" ብለዋል።
ይህ ከመገለጹ ቀደም ብሎ ዲሞክራቱ እንደራሴ ግሪጎሪ ሚክስ፤ በፕሬዚደንት ትራምፕ እና ፖምፒዮ በኩል ሌላ እንቅፋት የደቀኑት ሥልጣናቸውን አስረክበው ሲወጡ፤ የሚጣውን አዲሱን የባይደን አስተዳደር በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ተመራጩ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን እቅድ፤ ኩባ- አሜሪካዊያን ቤተሰቦቻቸውን እንዲጎበኙ እና ገንዘብ እንዲልኩ መፍቀድን ያካትታል።
ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ በ2015 ከኩባ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ መደበኛነት የመለሱ ሲሆን፤ አሜሪካ ለዘመናት አገሪቷን ለማግለል ያደረገችውን ጥረት "ውድቀት" ነው ሲሉ ነበር የገለፁት።
ከቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ጀምሮ አሜሪካ እንደ ትልቅ ስጋት ያየቻትን ኩባን ለማዳከም የተለያዩ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ አድርጋ ነበር።
አሁን በተላለፈው ውሳኔ መሰረትም ኩባ፤ ኢራንና ሰሜን ኮሪያ የተካተቱበት ሽብርን የሚደግፉት አገራትን ተቀላቅላለች።
ይህ ውሳኔ በደሴታማዋ አገር ላይ የውጭ ኢንቨስትመንትን ጨምሮ ከባድ ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሏል።












