ቻይና የትራምፕን ማዕቀብ ለመቋቋም አዲስ ሕግ ይፋ አደረገች

የቻይና ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና ኩባንያዎቿን "ትክክለኛ ካልሆኑ" ሕጎች የሚከላከሉ አዳዲስ ሕጎችን በማውጣት የአሜሪካ ማዕቀብን ለመከላለከል እየሠራች መሆኗ ተነገረ።

በሳምንቱ መጨረሻ ይፋ የተደረጉት ለውጦች የቻይና ፍርድ ቤቶች እንደዚህ ያሉ ገደቦች የሚመለከታቸው ኩባንያዎችን እንዲቀጡ ያስችላቸዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአሜሪካ ደኅንነት ስጋት ናቸው ያሏቸው የቻይና ኩባንያዎች ላይ ማነጣጠራቸውን ቀጥለዋል።

እርምጃዎቹ በጥቁር መዝገብ ላይ ከሰፈሩ ድርጅቶች ጋር የሚሠሩት መቅጣትን ያካትታሉ።

ሰኞ ዕለት በኒው ዮርክ የአክሲዮን ገበያ (NYSE) የተዘረዘሩ ሦስት ትልልቅ የቻይና የቴሌኮም ኩባንያዎች ከአገሪቱ ወታደራዊ ኃይል ጋር ግንኙነቶች አላቸው በሚል የአክሲዮን ድርሻቸውን እንዳይሸጡ ይከለከላል ተብሎ ይጠበቃል።

ትራምፕ ባስተላለፉት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ መሠረት የኒው ዮርክ የአክሲዮን ገበያ ቻይና ሞባይል፣ ቻይና ቴሌኮም እና ቻይና ዩኒኮም ሆንግ ኮንግ የተባሉት ድርጅቶች እያሰናበተ ነው።

በቅርብ ወራት እንደቲክቶክ፣ ሁዋዌ እና የማይክሮቺፕ አምራች የሆነው ሴሚኮንዳክተር ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን ጨምሮ በቻይና ኩባንያዎች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎችን ተከትሎ የመጣ ነው።

ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ታዋቂ የክፍያ ዘዴዎቹን አሊፔይን እና ዌቻት ፔይን ጨምሮ ከስምንት የቻይና መተግበሪያዎች ጋር ግብይቶችን ለማድረግ የሚያግደውን ትዕዛዝ ፈርመዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት መሰል የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መረጃዎችን ከቻይና መንግሥት ጋር እንደሚያጋሩ ቢገልጹም ኩባንያዎቹ ክሱን ውድቅ ያደርጋሉ።

የቻይና ንግድ ሚኒስቴር ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ የውጭ ሕጎችን "ተገቢ ያልሆነ የክልከላ አተገባበርን በመቃወም" ላይ አዲሱን ሕግ አስተዋውቋል።

በሲንጋፖር ዩኒቨርሲቲ የምሥራቅ እስያ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር የሆኑት በርት ሆፍማን "በውጭ ሕግ ምክንያት የተጎዱ ሕጋዊ አካላት በፍርድ ቤት ጉዳያቸውን በማቅረብ ለደረሰው ጉዳት ካሳ መጠየቅ ይችላሉ። መንግሥትም ሌሎች የመከላከያ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላል" ብለዋል።

የመልስ ምት

ቻይና በአሜሪካ ማዕቀብ እና በንግድ ላይ እገዳዎች ዙሪያ ለረዥም ጊዜ ቅሬታዋን ብትገልፅም ወደ ተግባር የገቡት እርምጃዎች በቀጥታ አሜሪካን አይጠቅሱም።

የሕግ ባለሙያዎች አዲሱ ሕግ እንዴት እንደሚተገበር ግልፅ አለመሆኑን ይናገራሉ።

የሕግ ባለሙያው ኒኮላስ ተርነር "ግልጽ መሆን የሚገባው አንድ ነጥብ ሕጉ በቻይና ላይ በተጣሉ ማዕቀቦች ላይ ያነጣጠረ ነው ወይስ እንደ ኢራን ወይም ሩሲያ ባሉ በሦስተኛ አገራት እና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድም ቻይናን በሚነኩ ማዕቀቦችም ላይ ተግባራዊ የሚሆን ነው የሚለው ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በቻይና ከፍተኛ የንግድ ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች በጥንቃቄ መመልከት ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

በሆንግ ኮንግ ዩኒቨርሲቲ የቻይና የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት አንጄላ ዣንግ "አንድ ሁኔታን እናንሳ፤ አንድ የአውሮፓ ባንክ በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበትን የቻይና ባለሥልጣን ንብረት እንዳይንቀሳቀስ ቢያደርግ፣ የቻይና ሕግ ባለሥልጣኑ የደረሰበትን ኪሳራ ለማስመለስ ባንኩን የመክሰስ መብት ይሰጠዋል" ብለዋል።

እንደተርነር ከሆነ ትራምፕ በዚህ ወር መጨረሻ ከዋይት ሐውስ ከመውጣታቸው በፊት ሊያመጡዋቸው ከሚችሏቸው የወደፊት ማዕቀቦች ቻይና ራሷን እየተከላከለች እንደሆነ ያምናሉ።

"ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በተሰጡ መግለጫዎች ላይ በመመስረት በጥቂት ቀናት ውስጥ ተጨማሪ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብዬ እጠብቃለሁ። የቀሩትን ቀናት ሁኔታውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ማንኛውንም አዲስ እገዳ ማወጣት መቻላቸው የሚታሰብ አይደለም" ብለዋል።