ኤፍቢአይ ትራምፕን የሚደግፉ ተጨማሪ ነውጦች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አስጠነቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ተሰናባቹን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን የሚደግፉ ነውጦች በመላው አሜሪካ ግዛቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ የአሜሪካው የፌደራል ምርመራ ቢሮ ኤፍቢአይ አስጠንቅቋል።
መጪው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም ሹመታቸውን ከሚረከቡበት ቀንም ቀድመው ሊከሰቱ እንደሚችሉ ቢሮው መረጃ ደርሶኛል ብሏል።
በጦር መሳሪያ የታገዙ ነውጦች ዋሽንግተን ዲሲን ጨምሮ በአምሳ የተለያዩ የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት መቀመጫዎች መታቀዳቸውን ሪፖርቶች ቢሮው አግኝቷል።
ጆ ባይደን ከስምንት ቀናት በኋላ በዓለ ሲመታቸው የሚካሄድ ሲሆን የዝግጅቱንም የፀጥታ ሁኔታ ለማስጠበቅ ከፍተኛ የደህንነት ስራዎች እየተሰራ ቢሆንም ፍራቻዎች ነግሰዋል።
በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ ላይም ጆ ባይደን ለሪፖርተሮች እንደተናገሩት የምክር ቤት አባላትና የመንግሥት ተሿሚዎች መቀመጫ ከሆነው የአሜሪካው ካፒቶል ህንፃ ውጭ ቃለ መሓላቸውንም ለመፈፀም እንደማያስፈራቸው ነው።
እሳቸውም ሆነ ምክትል ፕሬዚዳንቷ ካማላ ሃሪስ በትራምፕ ደጋፊዎች በቅርቡ በነውጠኞች ተከቦ ከፍተኛ አመፅ የተከሰተበት የካፒቶል ህንፃ ውጭ ቃለ መሓላቸውን እንዲፈፅሙ ይጠበቃሉ።
የምክር ቤቱ አባላት የምርጫውን ውጤት የመጨረሻ ማረጋገጫ ለመስጠት ድምፅ እየሰጡ በነበረበት ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ የምርጫውን ውጤት አንቀበልም ያሉ የትራምፕ ደጋፊዎች የካፒቶልን ህንፃ ሰብረው በመግባት ከፍተኛ ነውጥ አስከስተዋል።
የፀጥታ ኃይሎችም ከሳምንት በፊት የተከሰተው ይህ የሽብር ሁኔታ እንደገና እንደማይከሰት ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
የአሜሪካ ሆምላንድ ሴኩሪቱ ኃላፊ ቻድ ዎልፍ የመሪዎቹ በዓለ ሲመት ከመካሄዱ ቀደም ብሎም የአሜሪካ የደህንነት ልዩ ተልዕኮ እንዲያከናውንም ትዕዛዝ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
"በባለፈው ሳምንት የተከሰተውንና ያንዣበበውን የደህንነት ስጋት በማየት አስፈላጊ ሆኗል" ብለዋል።
የዝግጅቱንም ደህንነት ለመቆጣጠር 15 ሺህ የአሜሪካ ብሄራዊ ወታደሮችም ይሰማራሉ ተብሏል።
ሆኖም ትዕዛዝ ባስተላለፉባት በዚያችው ቀን በካፒቶል አመፁ ምክንያት ቻድ ዎልፍ ከስልጣናቸው እንዲነሱ ተደርገዋል።
በዚህ አመፅ ምክንያትም የተነሱ ሶስተኛው የምክር ቤት አባልም ሆነዋል። ቻድ ዎልፍ ነውጠኞቹን እንዲያወግዙም ለትራምፕ ጥሪ አቅርበው ነበር።












