ሠላማዊ ነዋሪዎች ሰለባ እየሆኑበት ያለው የኦሮሚያ ክልል ግጭት

ኪቲላ ጉደታ

የፎቶው ባለመብት, Kitilaa Guddata

የምስሉ መግለጫ, ኪቲላ ጉደታ

የኢትዮጵያ ፌደራል ሠራዊት በሁለት ሳምንት ውስጥ እንደሚደመስሰው የተናገረው በኦሮሚያ ክልል ያለው የአማጺ ቡድን እንቅስቃሴ በትግራይ ውስጥ ቀውስ በተከሰተበት ባለፉት ወራት ውስጥ ተባብሷል።

መረጋጋት በራቃቸው የኦሮሚያ ምዕራባዊና ደቡባዊ ክፍሎች ውስጥ መንግሥት ኦነግ-ሸኔ ብሎ ከሚጠራቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ኃይሎች ጋር ፍልሚያ ላይ ነው።

ይህ አማጺ ቡድን በቀደመው የኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኛ ድርጅት ተብሎ በሕገ ወጥነት በስደት ላይ የነበረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ወታደራዊ ክንፍ ነበር።

ቡድኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በርካታ የታጠቁና ያልታጠቁ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው።

ኦነግ ወደ አገር ቤት ከተመለሰ በጥቂት ወራት ውስጥ ታጣቂ ኃይሉን ትጥቅ በማስፈታት ከአገሪቱ ሠራዊት ጋር በሚዋሃድበት መንገድ ላይ አጠቃላይ ስምምነት ለመድረስ ሳይችል ቀረ። ኋላ ላይም የቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ ከፓርቲው በመለየት የትጥቅ ትግሉን እንደሚቀጥል አስታወቋል።

ከዚህም በኋላ ከመንግሥት ወታደሮች ጋር ምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ ሲዋጉ ግጭቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

በትግራይ ክልል ውስጥ ወታደራዊ ግጭት ከተከሰተ በኋላ አማጺ ቡድኑን የመቆጣጠሩን ኃላፊነት የተረከበረው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ለአንድ ወር ባካሄደው ዘመቻ ከ350 በላይ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎችን መግደሉንና ከ170 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ መያዙን ታኅሣስ 10/2013 ዓ.ም ላይ አስታውቋል።

በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በትግራይ ክልል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ተቋርጠዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች የክልሉን ልዩ ኃይል ከሕግ ውጪ ሠላማዊ ሰዎችን በመግደል ይከሳሉ።

የ32 ዓመቱ የሁለተኛ ደረጃ መምህር ኪቲላ ጉደታ በምዕራብ ኦሮሚያ ሆሮ ጉድሩ ዞን ውስጥ በልዩ ኃይል ፖሊሶች ተገድለዋል ከሚባሉት ሰዎች መካከል አንዱ ነው።

ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሟች ቤተሰብ አባል ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ኪቲላ ኅዳር ሐሙስ 10/2013 ዓ.ም ከ10 በላይ በሚሆኑ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ አባላት ምሽት 3፡30 ላይ ሰከላ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው ቤቱ ነበር የተወሰደው።

"የሁለት ልጆቹ እናት የሆነችው ባለቤቱ ከእሱ ይልቅ እሷን እንዲወስዷት ለምናቸው ነበር፤ ነገር ግን ከተወሰኑ ጥያቄዎች በኋላ ተመልሶ እንደሚመጣ ነገሯት" ብሏል።

ቤተሰብ ኪቲላን በሚቀጥለው ቀን ቢፈልገውም የትም ሊገኝ አልቻለም። ስልኩም እንደተዘጋ ነበር።

"አርብ ዕለት ምሽት 1 ሰዓት አካባቢ እንደተገደለ አንዳንድ ሰዎች ነገሩን፤ ነገር ግን አስከሬኑን ልናገኝ አልቻልንም" ብሏል።

"ቅዳሜ ጠዋት ሃሮ አጋ ተብሎ በሚታወቀውና ከከተማዋ ወጣ ብሎ ከሚገኝ ቦታ ላይ አስከሬኑ እንደታየ ሰማን፤ እኔ ነበርኩ ቦታው ላይ ቀድሜ የደረስኩት።"

"በወንዝ አቅራቢያ ባለ አለት ላይ ነው ተገድሎ ያገኘነው። እጁ ወደኋላ ታስሮ ከኋላው ተተኩሶበት ነበር የተገደለው። የተኩስ መለማመጃ ያደረጉት ነበር የሚመስለው" ሲሉ ዘመዱ ተናግሯል።

ቤተሰቦቹ እንዳሉት ከኪቲላ ጋር የሌሎች ሁለት ሰዎች አስከሬንም ተገኝቷል። በኋላ ላይ የሁለቱ ማንነት የተለየ ሲሆን አንደኛው በመንግሥት መሥሪያ ቤት ጥበቃ የነበረው ጋዲሳ አለማየሁ የተባለ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የጉልበት ሠራተኛው ብርሃኑ ገበየሁ ነው። ሁለቱም የከተማዋ ነዋሪዎች ናቸው።

የኪቲላ ጉደታ ቤተሰቦች እንደሚሉት አስካሁን እንዴትና ለምን እንደተገደለ የተነገራቸው ነገር የለም። ኪቲላ ቀደም ሲል የኦነግ ደጋፊ ነህ ተብሎ በተደጋጋሚ ታስሮ ተፈትቶ ነበር።

ስለቀረቡት የግድያ ክሶች ከኦሮሚያ ልዩ የፖሊስ ኃይል ምልሽ ለማግኘት ያደርግናቸው ጥረቶች አልተሳኩም። ነገር ግን የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ባልቻ፤ ከአማጺው ቡድን እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የሠላማዊ ሰዎችን ሞት ለመከላከል መንግሥት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"እርምጃ የተወሰደባቸው ወንጀላቸው በታወቀና በሕዝቡ በተጋለጡት ላይ ብቻ ነው" ብለዋል።

"በሠላማዊ ሰዎች ላይ ስለተፈጸመ ግድያ የማውቀው ነገር የለም። ነገር ግን የፖሊስ አባላትም ሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወንጀል ፈጽመው ከተገኙ ተጠያቂ ይሆናሉ" ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

ኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ ኃይል አባላት

የፎቶው ባለመብት, Oromia Police Commission/Facebook

የምስሉ መግለጫ, ኦሮሚያ ልዩ ፖሊስ ኃይል አባላት

'ለምን እንደገደሉት አናውቅም'

አንዳንዶቹ ግድያዎች የተፈጸሙት የአማጺ ቡድኑ እንቅስቃሴ በሌለባቸው ቦታዎች ጭምር ነው።

አርብ ኅዳር 10/2013 ዓ.ም ኪቲላ ከቤቱ ከተወሰደ በኋላ ባለው ቀጣይ ምሽት ተመሳሳይ ነገር በአርባዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኘው ገላና ኢማና ላይ እንደተፈጸመ ቤተሰቦቹ ይናገራሉ።

የሁለት ልጆች አባት የሆነው ገላና ነዋሪነቱ ከአዲስ አበባ 100 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በአምቦ ከተማ ነበር። ምሽት አራት ሰዓት አካባቢ 20 በሚደርሱ የታጠቁ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊሶች ከቤቱ ተይዞ ተወሰደ።

ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ የምትኖረው ታናሽ እህቱ ጫልቱ ኢማና ወንድሟ መያዙን ስትሰማ ቅዳሜ ዕለት ወደ አምቦ መሄዷን ለቢቢሲ ተናግራለች።

ለሁለት ቀናትም በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ እስር ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች ወንድሟን ብትፈለግም ልተገኘው አልቻለችም ነበር።

"ዕሁድ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊሶች ወደሚገኙበት ካምፕ ሄጄ በር ላይ ያገኘሁትን ሰው ወንድሜ የት እንዳለ እንዲነግረኝ ለመንኩት። ስሙንም ስነግረው ያለበትን ቦታ በመፈለግ እንዳልደክም መከረኝ።

"እንደማላገኘውም ነገረኝ። ወንድሜ ከከተማዋ ውጪ ወደሚገኝ የተሃድሶ ስልጠና መስጫ እንደተላከና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለቤተሰቡ የት እንዳለ ይነገራል" አለኝ።

ሰኞ ምሽት ኅዳር 14/2013 ከከተማዋ ወጣ ብሎ በሚገኝና ዳቢስ ተብሎ በሚጠራ ወንዝ አካባቢ ፖሊስ የሞተ ሰው አግኝቶ መቅበሩን የሚገልጽ ወሬ ቤተሰቡ መስማት ጀመረ።

ጫልቱም በሚቀጥለው ቀን ማክሰኞ ፖሊስ አግኝቶ ስለቀበረው ግለሰብ ማንነት ለማወቅ ወደ አካባቢው ፖሊስ ጣቢያ ሄደች።

"ከብዙ ንግግር በኋላ ፎቶውን እንድናመጣና በተያዘበት ጊዜ ለብሶት የነበረውን የልብስ አይነት እንድንነግራቸው ጠየቁን። በኋላም ከሰጠናቸው መረጃ ተነስተው የቀበሩት ግለሰብ ከወንድሜ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ አረጋገጡ" ትላለች።

"ከዚያም አስከሬኑ ሳይኖር ወደ ቤታችን ሄደን ሐዘን እንድንቀመት ነገሩን። ምንም ምርጫ አልነበረንም።"

በተጨማሪም ወንድሟ በጥይት ተመቶ መገደሉን ፖሊሶቹ እንደነገሯትና ከመቀበሩ በፊት ለቤተሰቡ ያላሳወቁት አድራሻቸውን ስላላወቁ መሆኑን ተናግረዋል።

"መያዙን ብቻ ነው የምናውቀው። ምን ወንጀል እንደፈጸመና ፍርድ ቤት ከማቅረብ ይልቅ ለምን መግደል እንደመረጡ የምናውቀው ነገር የለም" ትላለች ጫልቱ።

ወንድሟ ቀደም ሲል የኦነግ መሪዎች ወደ አገር ቤት ሲመለሱ በአቀባበል ኮሚቴ ውስጥ በመግባት ማገልገሉን እህቱ ታስታውሳለች።

'ሠላማዊ ሰዎች ዋጋ እየከፈሉ ነው'

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በኅዳር ወር ብቻ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በጸጥታ ኃይሎች ተገደሉ የተባሉ 12 ሰላማዊ ሰዎችን እንደመዘገበ ይናገራል።

ኮሚሽኑ እንደሚለው ጥቅምት 13/2013 ዓ.ም ምሥራቅ ወለጋ ነቀምቴ ውስጥ በአንድ ቤት ውስጥ የተገደሉ የአምስት ወጣቶችን ጉዳይ ጨምሮ በተወሰኑት ግድያዎች ላይ ምርመራ እያደረገ ነው።

"እንደ ኮሚሽን የተገነዘብነው ነገር ቢኖር በኦሮሚያ ውስጥ ፖለቲካዊ አለመግባባት ሠላማዊ ሰዎችን ውድ ዋጋ እያስከፈላቸው ነው" ሲሉ የኮሚሽኑ አማካሪ ኢማድ አብዱልፈታህ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እሳቸው እንዳሉት ግድያው የሚፈጸምበት መጠን "በጣም አሳሳቢ" እንደሆነ ገልጸው ሠላማዊ ሰዎች ኢላማ የሚደረጉት በመንግሥት ኃይሎች ብቻ ሳይሆን በአማጺያኑም ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ ሆሮ ጉድሩ ውስጥ አባይ ጮመን በተባለው ወረዳ ነዋሪ የሆኑ ሁለት የዓይን እማኞች በኅዳር 29/2013 ዓ.ም ላይ ሰባት ሠላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እንደተመለከቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ማክሰኞ ምሽት በድምጽ ማጉያ ለአስቸኳይ ስብሰባ የሚደረግ ጥሪ ሰማን" ይላሉ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉት የአካባቢው ነዋሪ።

"ስምንት ጸጉራቸው ረዥምና ፊታቸውን የሸፈኑ ታጣቂዎች፤ ከተሰበሰበው ሰው መካከል አማራዎች የሆኑ እራሳቸውን እንዲያሳውቁ ከጠየቁ በኋላ ቀሪዎቻችንን ወደ ቤታችን እንድንሄድ ነገሩን። ከዚያም 10 የሚሆኑትን ይዘዋቸው ሄዱ።"

"ተለቀው ይመጣሉ ብለን ሌሊቱን በሙሉ ብንጠብቅም ሳይመጡ ቀሩ። በሚቀጥለው ቀንም የሰባቱን አስከሬን አገኘን" ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ታጣቂዎች በሆሮ ጉድሩ ውስጥ አሙሩ በሚባለው ወረዳ ውስጥ 14 አማራዎችን እንደገደሉ አቶ ጌታቸው ባልቻ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢሬቻ በዓል ላይ የተሳተፉ ፈረሰኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

'ባንኮች ተዘርፈዋል፣ አምቡላንስ ተቃጥሏል'

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወለጋ ሆሮ ጉድሩ ውስጥ በታጣቂዎች የሚፈጸመው ጥቃት ካለፈው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ምናልባትም በብዛቱ የማይወዳደርና ያልተነገረ ነው።

በታኅሣስ ወር መጀመሪያ ላይ ታጣቂዎች ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ አካባቢ በምትገኘው ሐጋማሳ በምትባል መንደር ውስጥ የሚገኙ ሁለት ባንኮችን እንደዘረፉ ነዋሪዎችና የባንክ ባለሙያዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል። ምን ያህል ገንዘብ እንደተዘረፈ ግን የታወቀ ነገር የለም።

በዚህ ክስተትም የዞኑ ዋና ከተማ በሆነችው ሻምቡ ውስጥ የሚገኙ ባንኮች ተመሳሳይ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል በሚል ስጋት ከአንድ ቀን በላይ ተዘግተው አገልግሎት ሳይሰጡ ቆይተዋል።

በተጨማሪም ከሻምቡ ከተማ አቅራቢያ በምጥ የተያዘችን እናት ሐኪም ቤት አድርሶ የሚመለስ አምቡላንስና የግል ትራንስፖርት ተሽከርካሪ በታጣቂዎቹ በእሳት ተቃጥሏል።

"ታጣቂዎቹ ሚኒባሱን በእሳት ከመለኮሳቸው በፊት ከተሳፋሪዎቹ ላይ የሞባይል ስልኮችንና ገንዘብ ወስደዋል" ሲል አንድ የሻምቡ ከተማ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ወደ አዲስ አበባ ይጓዝ በነበረ አውቶብስ ላይ በታጣቂዎቹ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ለጥቂት ቀናት ወደ አገሪቱ ዋና ከተማዋ የሚደረግ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ ነበር።

ከፊንጫ ስኳር ፋብሪካ አቅራቢያ አዲስ በተከፈተ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉ አንድ ቄስም ታኅሣስ 08/2013 ዓ.ም በታጣቂዎቹ መገደላቸውን ፋብሪካው ውስጥ የሚሰራ ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት ጭምር የታጣቂዎቹ ጥቃት ኢላማ የሆኑባቸው ግድያዎች ምክንያት ግልጽ አይደለም። ባለስልጣናቱም ምላሽ እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት ሊሳካ አልቻለም።

ነዋሪዎች እንደሚሉት ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከስኳር ፋብሪካው አቅራቢያ ተኩስ ይሰማ እንደነበር ገልጸው፤ ይህም በታጣቂዎቹና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የሚደርግ የተኩስ ልውውጥ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

በባንኮች ላይ ለደረሱ ዘረፋዎች፣ በመንግሥት ባለሥልጣናትና በሠላማዊ ዜጎች ለተፈጸሙ ግድያ ኦነግ-ሸኔ ብሎ የሚጠራውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን መንግሥት በተደጋጋሚ ይከሳል።

መንግሥት ጨምሮም ታጣቂው ቡድን በህወሓት እየተደገፈ አገሪቱ እንዳትረጋጋ ለማድረግ እየሞከረ ነው ይላል። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ግን ይህንን ክስ ያስተባብላል።

ባህላዊው መሪ አባ ገዳ ኩራ ጃርሶ

የፎቶው ባለመብት, Eric Lafforgue/Art in All of Us

የምስሉ መግለጫ, ባህላዊው መሪ አባ ገዳ ኩራ ጃርሶ

'የሕዝብ ጠላት'

መንግሥት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት በትግራይ ውስጥ ወታደራዊ ግጭት ከመቀስቀሱ ከሦስት ቀናት ቀደም ብሎ 34 ሠላማዊ ሠዎች በጉሊሶ ወረዳ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ለስብሰባ ተብለው ከተጠሩ በኋላ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ተገድለዋል።

ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች እንደተናገሩት በታጣቂዎች በተከፈተባቸው ተኩስ እዚያው ቦታው ላይ ቢያንስ 34 የአማራ ብሔር ተወላጆች ተገድለዋል።

ለሁለት ዓመታት ያህል በዘለቀው በዚህ የአማጺያን እንቅስቃሴ ወቅት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ የሚያመለክት ግልጽ አሃዝ የለም።

ነዋሪዎች እንደሚሉት አማጺያኑን በመዋጋት በአካባቢው ሰፍሮ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት በድንገት ለቆ መውጣቱ በታጣቂዎቹ ለሚፈጸመው ጥቃት እንዳጋለጣቸው ገልጸዋል።

የተፈጸሙትን ግድያዎች ተከትሎ የኦሮሚያ ፖሊስ በወሰደው የአጸፋ እርምጃ 142 ታጣቂዎችን መግደሉን ኅዳር 09/2013 ዓ.ም አስታውቋል።

ምንም እንኳን መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ታጣቂዎችን መግደሉን ቢያስታውቅም ውጊያው የተጠናቀቀ አይመስልም።

የአሁኑ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ምክትል በነበሩበት ጊዜ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ሠራዊቱ አብዛኛውን ምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያን ከአማጺያኑ ነጻ ማውጣቱንና "የቀሩት ተወሰኑ ታጣቂዎች" መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ነገር ግን የአማጺያኑ እንቅስቃሴ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየሰፋ መምጣቱን የክልሉ ፖሊስ በቅርቡ በማዕከላዊና በምሥራቃዊ የኦሮሚያ አካባቢዎች ውስጥ ታጣቂዎችን እንደገደለ መግለጹ አመላካች ሊሆን ይችላል።

በደቡባዊ ኢትዮጵያ የቦረና አካባቢ የአማጺው ታጣቂዎች ከአንድ ወር በፊት አንድ ህጻን በመግደላቸው ቡድኑ የአካባቢው ባህላዊ መሪ በሆኑት በአባ ገዳ ኩራ ጃርሶ "የሕዝብ ጠላት" ተብሎ ተወግዟል።

ታጣቂዎቹ ለረጅም ጊዜ ሲንቀሳቀሱበት በነበረው ኢትዮጵያና ኬንያ በሚዋሰኑበት የቦረና አካባቢ ሠላማዊ ሰዎችን ሲገድሉ፣ ሴቶችን ሲደፍሩና ከብቶችን ሲዘርፉ ቆይተዋል ሲሉ አባ ገዳ ኩራጃርሶ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከፕሬዝደናት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ኅዳር 30/2013 ዓ.ም የኢትዮጵያና የኬንያን የድንበር መተላለፊያ መርቀው በከፈቱበት ጊዜ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ከአል-ሻባብ ጋር አብረው ጠቅሰውታል።

ጨምረውም የሕዝቡን ህይወት ለመቀየር ሁለቱ አገራት ኦነግ-ሸኔን እና አል-ሻባብን ከአካባቢው ለማጥፋት በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።