ኢራን ከፍተኛ ጥራት ያለው ዩራኒየም ማበልጸግ መጀመሯን አስታወቀች

ዩራንየም 20% ጥራት ልታበለጽግ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA

ኢራን ከአምስት ዓመት በፊት ከኃያላን አገራት ጋር ያደረገችውን የኒውክሌር ስምምነት በተጻራሪ ዩራኒየም በ20 በመቶ የጥራት ደራጃ ማበልጸግ መጀመሯን አስታወቀች።

የኢራን መንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት አሊ ራቢ እንዳሉት ቃም አቅራቢያ ከመሬት በታች በሚገኘው ፎርዶ የኒውክለር ተቋም ሂደቱ መጀመሩን ለመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

የበለፀገ ዩራኒየም የማብላያ ነዳጅ ብቻ ሳይሆን የኑክሌር ቦምቦችን ለማምረትም ሊያገለግል ይችላል። በጦር መሳሪያዎች ደረጃ የሚያገለግለው ዩራኒየም 90 በመቶ ድረስ መበልጸግ አለበት።

የኒውክሌር ፕሮግራሟ ሠላማዊ መሆኑን የምትገልጸው ኢራን የአሜሪካንን ማዕቀብ ተከትሎ ከስምምነቱ በተጸራሪ በርካታ አርምጃዎችን በመውሰድ ወደ ኋላ ተመልሳለች።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የኢራን ውሳኔ "ወታደራዊ ኒውክሌር የማዘጋጀት ዓላማዋን ከመቀጠል በስተቀር በሌላ መንገድ ሊገለፅ አይችልም" ብለዋል።

አክለውም "እስራኤል ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንድትሠራ በፍጹም አትፈቅድም" ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ራቢ ለኢራን የዜና ወኪል ኢርና እንደተናገሩት የዩራኒየም መጠን ወደ 20 በመቶ የማበልፀግ ሂደት በፎርዶ ዛሬ መጀመሩን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሩሃኒ እርምጃውን ያዘዙት ለሠላማዊ ዓላማ በዓመት ቢያንስ 120 ኪሎ ግራም እስከ 20 በመቶ የበለፀገ የዩራኒየም ማምረት እና ማከማቸት ለሚፈወቅደው አዲስ ሕግ "ተገዥ" በመሆናቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢራን ፓርላማ ሕጉን ያፀደቀው ባለፈው ሳምንት እስራኤልን ተጠያቂ ባደረገበት እና የአገሪቱ ከፍተኛ የኑክሌር ሳይንቲስት ሞህሰን ፋክህሪዛድ መገደላቸውን ተከትሎ ነው።

የዓለም አቀፉ የአቶውሚክ ኢነርጂ ድርጅት ተቆጣጣሪዎች በፎርዶ የተከናወኑ ተግባራትን እየተከታተሉ ሲሆን ሪፖርት ለአባል አገራት እንደሚያቀርብም አስታውቋል።

ነገር ግን ዓለም አቀፉ ጥበቃ ድርጅት ባለፈው ሳምንት ወደ 20 በመቶ ለማበልፀግ ስለነበራት ዕቅድ ከኢራን መረጃ እንዳገኘ ገልጿል።

የበለፀገ ዩራኒየም ምንድነው?

ዩ-235 ተብሎ ለሚጠራው ኒውክሌር በጣም ተስማሚ የሆነውን አይዞቶፕ ለመለየት የዩራኒየም ሄክሳፍሎራይድ ጋዝን ወደ በማዋሃድ ሂደት የበለፀገ ዩራኒየም ይመረታል።

በዝቅተኛ ደረጃ የበለፀገ የዩራኒየም መጠን ከ3-5 በመቶ ዩ -235 ያለው ሲሆን ለኒውክሌር ኃይል ማመንጫዎች ነዳጅ ለማምረት ስለሚያገለግል ለንግድ ሊውል ይችላል።

በከፍተኛ ደረጃ የበለፀገ የዩራኒየም መጠን 20 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ ጥራት ያለው ነው።

በኒውክሌር ስምምነት መሠረት ኢራን ዩራኒየምን እስከ 3.67 በመቶ ብቻ ማበልጸግ እና ከ300 ኪ.ግ የማይበልጥ ለማከማቸት ተፈቅዶላት ነበር።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በ2018 (እአአ) ስምምነቱን በመተው ኢራን ላይ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ በመጣላቸው አገሪቱ ስምምነቱን ወደ ጎን በማለት "እርምጃዎችን ወስዳለች።

አሜሪካ ለስምምነቱ ተገዢ ከሆነች አብራ ለመስራት እንደምትችል ኢራን አስታውቃለች።