ኢራን ከስምምነት ውጪ ከፍተኛ ጥራት ያለው ዩራኒየም ልታበለጽግ ነው ተባለ

ዩራንየም 20% ጥራት ልታበለጽግ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA

ኢራን ዩራኒየምን በ20 በመቶ ጥራት ለማበልጸግ እንዳቀደች የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ። ይህም ከፍተኛ የዓለም አቀፍ ኒውክሌር ስምምነት ጥሰት ነው ብሏል።

ይህም ኒውክሌር ቦምብ ለመሥራት ከሚፈለገው 90 በመቶ ያነሰ ቢሆንም፤ እአአ 2015 ላይ የተደረገው ስምምነት ኢራን የምታበለጽገው ዩራኒየም ደረጃ ከ4 በመቶ እንዳይበልጥ ይደነግጋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአውቶሚክ ተቆጣጣሪ ክፍል እንደሚለው፤ ይህ የኢራን ውሳኔ ኒውክሌርን የተመለከተ ዓለም አቀፍ ስምምነትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጥስ ነው።

ኢራን ስምምነቱን መጣስ የጀመረችው ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በኋላ ማዕቀቦችን በድጋሚ መጣል በመጀመራቸው ነው።

ሆኖም ግን ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ ሩሲያ እና ቻይና ይህ ይቀለበሳል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።

ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (አይኤኢኤ) እንደተናገረው፤ ኢራን በተራራማ አካባቢ በሚገኘው ፎርዶው ፊውል የተባለ የዩራኒየም ማበልጸጊያ ተቋም፤ ዩራንየምን በ20 በመቶ ጥራት የማበልጸግ እንቅድ እንዳላት መረጃ ሰጥታለች።

"ኢራን በላከችው ደብዳቤ መቼ ዩራኒየሙ እንደሚበለጽግ አልገለጸችም" ብሏል ኤጀንሲው።

ኢራን ዩራኒየም የምታበለጽግበት መጠን ጣሪያው 3.67 በመቶ እንዲሆን 2019 ላይ ስምምነት ተደርጎ ነበር።

የኢራን ምክር ቤት ወደ 20 በመቶ የማሳደግ ውሳኔን ያስተላለፈው ባለፈው ወር ነው። ውሳኔው የኢራኑን የኒውክሌር ሳይንቲስት ግድያ ተከትሎ ነበር የጸደቀው።

በሁለት ወራት ውስጥ በኢራን ነዳጅና የፋይናንስ ዘርፍ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ካልተነሱ ዩራኒየምን 20 በመቶ ጥራት እንድታበለጽግ ምክር ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል።

የተባበሩት መንግሥታት መርማሪዎች በናታንዝ እና ፎርዶው ያሉ የኢራን ኒውክሌር ማበልጸሚያዎችን መፈተሽ እንዲያቆሙም ምክር ቤቱ አሳስቧል።

ዝቅተኛ ደረጃ ያለው ዩራኒየም (ከ3 እስከ 5 በመቶ) ከኒውክሌር ኃይል ለማመንጨት ሲውል፤ በከፍተኛ ጥራት የሚበለጽግ ዩራኒየም (20 በመቶ) መሣሪያ ለማምረት ይውላል።

ተንታኞች እንደሚሉት፤ ኢራን ዩራኒየምን በጥራት ማምረት ከጀመረች ኒውክሌር ቦምብ ለመሥራት የሚወስድባትን ጊዜ ያሳጥረዋል።

2010 ላይ የአውሮፓ ሕብረት፣ አሜሪካ እና የተባበሩት መንግሥታት ኢራን ላይ ማዕቀብ የጣሉት ኒውክሌር ቦምብ እየሠራች ነው በሚል ጥርጣሬ ነው።

2015 ላይ ከቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ጋር የተደረገው ስምምነት የኒውክሌር ፕሮግራም እንዲገታና በምላሹ ማዕቀቦች እንዲነሱ የሚያደራድር ነው።

ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በ2018 ስምምነቱን "ያረጀ ያፈጀ" ብለው አሜሪካን አስወጥተዋል።

ጥር 20 በይፋ ሥልጣን የሚረከቡት ቀጣዩ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን አሜሪካን ወደ ስምምነቱ እንደሚመልሱ ተናግረዋል።

"ኒውክሌር ቦምብ በዚያ አካባቢ እንዲገነባ አንፈልግም" ማለታቸውን ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

ኢራን ለስምምነቱ ለመገዛት አሜሪካም የድርሻዋን እንድትወጣ እንደምትፈልግ አስታውቃለች።

"ባይደን ስምምነቱ 2017 ላይ እንደነበረው የሚመልሱ ከሆነ እኛም እንመለሳለን" ብለዋል የኢራኑ ፕሬዝዳንር ሐሰን ሮሀኒ።