ቴክኖሎጂ፡ ጉግል ማሳዎችን መከታተል የሚችሉ ሮቦቶችን እየሰራ ነው

ፀሃይ ስትገባ የሚያሳይ ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Mineral

የጉግል አባት ድርጅት የሆነው አልፋቤት በማሳ ላይ በመሰማራት የእያንዳንዱን ተክል ሁኔታ መከታተል የሚችሉና የገበሬዎችን ሕይወት ማቅለል የሚችሉ ሮቦቶችን ለሙከራ ማቅረቡ ተሰምቷል።

ሮቦቶቹ ከላይ ሆነው ተክሎቹን መከታተል የሚችሉ ሲሆኑ የተክሎቹን ተፈጥሮአዊ እድገትና ሁኔታ በማይነካ መልኩ ስራቸውን መስራት እንደሚችሉ ተገልጿል።

ድርጅቱ እንዳስታወቀው ዋነኛው አላማቸው ተክሎችን በተመለከተ በቂና አስተማማኝ መረጃ መሰብሰብ ነው።

የፕሮጀክቱ መሪ የሆኑት ኤሊየት ግራንት ሲናገሩ '' እነዚህ ሮቦቶች የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ወደፊት የሚኖረንን የግብርናዘዴ ዘመናዊ እንደሚያደርገው እምነታችን ነው'' ብለዋል።

የምርምር ቡድኑ እንደገለጸው እነዚህን ሮቦቶች ወደ ሙከራ ማሰገባት ያስፈለገው በዓለም ላይ ያለውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍና ዘላቂ በሆነ መልኩ የግብርና ውጤቶችን ለማዳረስ ነው።

ነገር ግን አሁን ላይ ገበሬዎችና ትልልቅ የግብርና ድርጅቶች ያሏቸው መሳሪያዎች ይህንን ለማድረግ አላስቻሏቸውም።

"እያንዳንዱ ተክል ምን ያክል ውሃና ንጥረነገር እንደሚያስፈልገው ማወቅ ከቻልንና የትኛው የተክል አይነት በየትኛው ቦታ ተመችቶች ያድጋል አልያም ይባዛል የሚለውን ጥያቄ መመለስ ከቻልን ግብርናችንን ውጤታማ በሆነ መልኩ ቀየርነው ማለት ነው'' ይላሉ የፕሮጀክቱ መሪ።

ከዚህ በተጨማረም ሮቦቶቹ ስለ አፈርና በአፈር ውስጥ ስላሉ አስፈላጊ ንጥረነገሮች በቂ መረጃ መስጠት የሚችሉ ሲሆን ተክሎቹም ቢሆኑ በምን ያክል ፍጥነት እያደጉ እንደሆነ ማሳየት ይችላሉ።

'' ባለፉት ጥቂት ዓመታት በካሊፎርኒያ እና ሶይቢን በሚገኙ የእንጆሪ ማሳዎች ላይ የተሞከሩ ሲሆን ሮቦቶቹ በጣም ጥርት ያለ ምስል ስለተክሎቹ ማግኘት እንድንችል አድርገውናል።

ምን ያክል ንጥረነገር እንደተጠቀሙና የጸሀይ ብርሃን ምን ያክል እንደሚያስፈልጋቸውም ጭምር መረጃ ማግነት ችለናል'' ብለዋል።

ከነዚህ ሮቦቶች ጋር የሚነሳው አንድ የጎንዮሽ ጉዳት የበይነ መረብ መረጃ ደህንነት ነው። መንግሥታት መረጃው እንዴት እንደሚሰበሰብና ጥቅም ላይ እንደሚውል ማወቅና መቆጠጠር መፈለጋቸው አይቀርም።

ድርጅቱ እንደሚለው ከአሁኑ ከአርጀንቲና፣ ካናዳ፣ ደቡብ አፍሪካ እና አሜሪካ ገበሬዎችና ዘር ማዳቀል ላይ ከተሰማሩ ሰዎች ጋር መስራት እንደጀመረም አስታውቋል።