ኮሮናቫይረስ ፡ "መተቃቀፍ ናፍቆናል" ኮቪድ-19 ያደናቀፈው የእናትና ልጅ ትስስር

ክላውዲያ ሃመንድ እና ባሏ ቲም
የምስሉ መግለጫ, ክላውዲያ ሃመንድ እና ባሏ ቲም

ለመጨረሻ ጊዜ ከሚወዱት ሰው ጋር የተቃቀፉት መቼ ነበር? ሰዎችን ማቀፍ በጣም ከናፈቀዎት ስሜቱ የእርስዎ ብቻ አይደለም።

መተቃቀፍ እና ሌሎችም ሰዋዊ ንክኪዎች የጤናማ ሥነ ልቦና መገለጫ እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ። ኮቪድ-19 ግን ከምንወዳቸው ሰዎች በአካል እንድንርቅ ምክንያት ሆኗል።

"ፊልም ወይም ሙዚቃ ከፍቼለት ፊቱን ዳብሰው ነበር"

"መተቃቀፍ ናፍቆናል" ከሚሉት አንዷ ሻረን ናት።

ሻረን፤ ሮብ የሚባል ልጅ አላት። በ25 ዓመቱ የሞተር ብስክሌት አደጋ ገጥሞት አእምሮው ስለተጎዳ በእንክብካቤ መስጫ ውስጥ ይገኛል።

ከአደጋው በኋላ ሮብ የሰው ልጅ ንክኪ እንደሚያስፈልገው ሻረን ተነግሯታል። ወረርሽኙ ከተከሰተ ወዲህ ግን ልጇን መደባበስ አልቻለችም።

"ፊልም ወይም ሙዚቃ ከፍቼለት ፊቱን አዳብሰው ነበር። አቅፈው፣ እስመውም ነበር።"

ባለፉት ስድስት ወራት ልጇን መንካት የቻለችው ሦስት ጊዜ ብቻ ነበር። ከላይ እስከ ታች በጭምብል ተሸፍና ጥፍሩንና ፀጉሩን ቆርጣለታለች፤ አቅፋዋለች።

የወረርሽኙ ስርጭት ሲሰፋ ግን ልጇን መጎብኘት እንኳን አልቻለችም።

"ልጄን ማቀፍና መሳም አለመቻሌ የሞት ያህል ነው። ማግኘት የምችለው በስልክ ብቻ ነው። አልያም ፎቶውን አያለሁ። በጣም ያሳዝናል።”

አካላዊ ርቀት በተለይም በእንክብካቤ መስጫ ላሉ ሰዎች ከባድ ነው።

ከወረርሽኙ በፊት መተቃቀፍን እንደ ቀላል ነገር ይወስዱ የነበሩ ሰዎች ሳይቀሩ አሁን ላይ ከሰው ጋር መነካካት ናፍቋቸዋል።

ሙኒክ የምትገኘው ፕሮፌሰር መርሊ ፌርሀርስት መተቃቀፍ ላይ ምርምር እያደረገች ነው። ሰዎች ለመጨረሻ ጊዜ የተቃቀፉበትን ጊዜ እንዲያስታውሱ ትጠይቅና ከዚያም ራሳቸውን ለሁለት ደቂቃ እንዲያቅፉ ትመክራለች።

ለንደን የሚኖሩ ደባሎች ቤተሰቦቻቸውን ማቀፍ ስለናፈቃቸው በየቀኑ 12 ሰዓት ላይ ለ25 ሰከንድ ብቻ ለመተቃቀፍ ተስማምተዋል።

ሌላው አማራጭ መጻፍ ነው። አንድ ሰው ሲያቅፉ ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መልዕክት በቃላት ለመግለጽ መሞከር ማለት ነው።

ክላውዲያ ሃመንድ
የምስሉ መግለጫ, ክላውዲያ ሃመንድ

"ጓደኛዬን የአባቷ ቀብር ላይ ሳላቅፋት ቀረሁ"

ክላውዲያ ሀመንድ የጓደኛዋ አባት ቀብር ላይ ተገኝታ ነበር።

የጓደኛዋ አባት አስክሬን አፈር ሲለብስ ጓደኛዋን ማቀፍ ብትፈልግም አልቻለችም።

ጓደኛዋን “አባትሽ እንደ ጓደኛችን ነበር። ደግ ነበር። አባትሽን ስላጣሽ አዝኛለሁ። አይዞሽ፤ ሁላችንም ከጎንሽ ነን” ብትላትም ከቃላት በላይ ትርጉም የሚኖረው ብታቅፋት እንደሆነ ታምናለች።

ኦፊሊያ ዲዮሪ ፈላስፋ ናት።

"አካላዊ ንክኪ ፍቅርን፣ ጓደኝነትን ይገልጻል። ፍላጎቱን መግታት አንችልም" ስትል ትገልጻለች።

ፕሮፌሰር ማይክል ባንሲ በተባሉ የሥነ ልቦና ተመራማሪ መሪነት የተሠራ የበይነ መረብ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያሳየው፤ በርካቶች ለመተቃቀፍ ቀና አመለካከት እንዳላቸው ይጠቁማል።

ከ112 አገሮች 40,000 ሰዎችን ያሳተፈው ጥናት እንደሚያሳየው መተቃቀፍ መፈለግ የጤናማነት ምልክት ነው። ብቸኝነት የማያጠቃቸው ሰዎች መተቃቀፍ ይወዳሉ።

ከጥናቱ ተሳታፊዎች 54 በመቶው የሰው ንክኪ ጎሎናል ሲሉ 3 በመቶ ደግሞ አካላዊ ንክኪ በዝቶብናል ብለዋል።

የ80 ዓመቱ ጆን ማርዮት ያደጉት በአያቶቻቸው እጅ ነው።

"አያቶቼ ቢወዱኝም አንድም ቀን አቅፈውኝ አያውቁም። ሁለቱም የተወለዱት በቪክቶሪያ ዘመን ስለነበር ልጆችን አይቅፉም" ይላሉ።

አዛውንቱ ልጅ ሳሉ የእድሜ እኩያቻቸውን ወላጆቻቸው ሲያቅፏቸው ሲያዩ ግራ ይጋቡ ነበር። ባለቤታቸውን ከተዋወቁ በኋላ ግን ነገሮች ተቀየሩ። የመተቃቀፍ ዋጋም ገባቸው።

ሁለቱ ሴት ልጆቻቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀፉበትን ወቅት የማይዘነጉት ጆን፤ ልጆቻቸውን፣ ስድስት የልጅ ልጆቻቸውን እንዲሁም የልጅ ልጅ ልጃቸውን እንደማቀፍ የሚያስደስታቸው ነገር የለም።

መተቃቀፍ

"መተቃቀፍ የማይወዱ ሰዎችም አሉ"

በበይነ መረብ የተሠራው ጥናት 27 በመቶ ሰዎች መተቃቀፍ እንደማይወዱ ያሳያል።

መተቃቀፍ ሁሉንም ሰው ጤናማ እንደማያደርግም አጥኚዎች ይናገራሉ።

መተቃቀፍ የሚወዱ ሰዎች ግልጽ ሲሆኑ፤ ሰው ማቀፍ የሚጠሉ ደግሞ ሰዎችን ማመን እንደሚቸገሩ ጥናቱ ያሳያል።

ዶክተር ኤሚ ካቫንጋህ የመብት ተሟጋች ናት። ሰዎች ያለፍቃዳቸው የሚነኩበት አጋጣሚ እንዳለ ትናገራለች።

አይነ ስውሯ ኤሚ በአንድ ቀን ውስጥ ቢያንስ አራት ሰው ያለፍቃዷ ይነካታል።

"ደረጃ ስወርድ ሰዎች ይመሩኛል፤ ወንበር ላይ እንድቀመጥ ይመሩኛል፤ ክንዴን ወይም ትከሻዬን የሚይዙኝ አሉ። ሌሎች በትሬን ይዘው ይመሩኛል። ሰውነቴ ላይ ምልክት ወይም ጭረት የሚቀርበት ጊዜም አለ።”

ሰዎች ሊረዷት ፈልገው እንደሆነ ብትረዳም ንክኪው መብቷን የሚጋፋ ሆኖም ይሰማታል። "አካል ጉዳተኛ ስለሆንኩ ሰዎች እኔን መንካት የሚችሉ ይመስላቸዋል" ስትል ስሜቷን ትገልጻለች።

አንዳንድ ሰዎች እርዳታ ሲያደርጉላት፤ ሌሎች በእርዳታ ሰበብ ወሲባዊ ትንኮሳ ያደርሱባታል።

በበይነ መረብ በተሠራው ጥናት መሠረት 63 በመቶ ሰዎች በማያውቁት ግለሰብ መነካት ደስ አይላቸውም። ከአዛውንቶች ይልቅ ወጣቶች በእንግዳ ሰው መነካት አይሹም።

ብዙዎች የማያውቁት ሰው ከእጃቸው ውጪ ሌላ የሰውነት አካላቸውን እንዲነካ አይፈቅዱም።

እንደ 'ሚቱ' አይነት ንቅናቄዎች አግባብ ስላልሆኑ ንክኪዎች ግንዛቤ አስፍተዋል። ሰዎችን ከመንካት በፊት ፍቃድ መጠየቅ አስፈላጊ መሆኑም እሙን ነው።

ኮሮናቫይረስ ልጇን እንዳታቅፍና እንዳትደባብሰው እንቅፋት የሆነባት ሻረን ልጇ ሮብን የምታቅፍበትን ቀን በጉጉት እየጠበቀች ነው።

“ይሄ ቫይረስ ሲወገድ ልጄን እንዴት እንደማቅፈው፣ ስንቴ እንደምስመው እኔ ነኝ የማውቀው” ትላለች።

ኮሮና
Banner