ለሁለተኛ ጊዜ በኮቪድ-19 የተያዘው ከመጀመሪያው በባሰ በጠና ታመመ

ኮሮናቫይረስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በኮሮናቫይረስ የተያዘው ሰው፤ ከመጀመሪያው በባሰ ሁኔታ በጠና መታመሙን ሐኪሞች ተናገሩ።

የ25 ዓመቱ ግለሰብ ከሳምባው በቂ ኦክስጅን ወደ ሰውነቱ መዘዋወር ስላልቻለ ሆስፒታል ገብቷል። በድጋሚ በቫይረሱ የመያዝ እድል አነስተኛ ሲሆን፤ ግለሰቡም እያገገመ ይገኛል።

የኔቫዳ ነዋሪ የሆነው ግለሰብ በተለየ ሁኔታ ለኮቪድ-19 ተጋላጭ የሚያደርገው ህመም ወይም በሽታ የመቋቋም ኃይል ውስንንነት የለበትም።

ግለሰቡ ከመጋቢት እስከ ሰኔ ድረስ ያሳየው የበሽታው ምልክቶች ቀጣዮቹ ናቸው፦

  • መጋቢት 25- የመጀመሪያው ዙር የበሽታው ምልክቶች ታየበት። ይህም የጉሮሮ መድረቅ፣ ሳል፣ ራስ ምታት፣ ድካምና ተቅማጥን ያካትታል።
  • ሚያዝያ 18- ለመጀመሪያ ጊዜ ቫይረሱ ተገኘበት።
  • ሚያዝያ 27- የመጀመሪያዎቹ የህመም ምልክቶች ሙሉ በሙሉ ተወገዱ።
  • ከሚያዝያ 9 እስከ ግንቦት 26- ሁለት ጊዜ ከበሽታው ነጻ መሆኑ ተረጋገጠ።
  • ግንቦት 28- ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ድካም፣ ሳል እና ተቅማጥን ጨምሮ በድጋሚ የበሽታውን ምልክት ማሳየት ጀመረ።
  • ሰኔ 5- ለሁለተኛ ጊዜ ቫይረሱ ተገኘበት። በሰውነቱ ውስጥ የኦክስጅን መጠን አነሰ፤ ትንፋሽም ያጥረው ጀመር።

ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ግለሰቡ ሁለት ጊዜ በቫይረሱ ተይዟል። መጀመሪያ የያዘው ቫይረስ ተደብቆ በድጋሚ አላገረሸበትም። የሁለቱ ቫይረሶች የዘረ መል ቅንጣት የተለያየ ነው።

በኔቫዳ ዩኒቨርስቲ መመህር የሆኑት ዶ/ር ማርክ ፓንዶሪ “ቀደም ያለ ኢንፌክሽን ለሁለተኛ ጊዜ በበሽታው ከመያዝ እንደማያድን ግኝታችን ይጠቁማል። ለሁለተኛ ጊዜ በቫይረሱ የመያዝ እድል መኖሩ በሽታን ስለመከላከል አቅም ያለንን አመለካከት ይለውጣል” ብለዋል።

ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ፣ እጃቸውን አዘውትረው መታጠብ እና አካላዊ ርቀት መጠበቅ እንዳለባቸውም ዶክተሩ መክረዋል።

ሳይንቲስቶች ገና ያልመለሷው ጥያቄዎች

ሁሉም ሰው በሽታውን የመከላከል አቅም ያዳብራል? መጠነኛ ምልክት ያሳዩ ሰዎች በሽታውን መከላከል ይችላሉ? በሽታውን የመከላከል አቅም ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል? የሚሉት ገና መልስ ያልተገኘላቸው ጥያቄዎች ናቸው።

በሽታው በጊዜ ሂደት የሚያሳድርብንን ተጽዕኖ ለመረዳት እንዲሁም ክትባት ለማግኘትም እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ያሻል።

እስካሁን በቫይረሱ ከተያዙ ከ37 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ዳግመኛ በሽታው የያዛቸው እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው።

ከሆንግ ኮንግ፣ ቤልጄም እና ኔዘርላንድ የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው፤ ለሁለተኛ ጊዜ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ከመጀመሪያው በበለጠ አልታመሙም። ኢኳዶር ውስጥ ግን ከመጀሪያው በላቀ የታመመ ሰው ነበር።

ሰውነት ቫይረሱን የመቋቋም አቅም ስለሚያዳብር ለሁለተኛ ጊዜ በሽታው ሲከሰት ቀለል ይላል የሚል መላ ምት ነበር። አሜሪካ ያለው ግለሰብ በሁለተኛው ዙር ለምን በሽታው እንደጠናበት አልታወቀም።

ምናልባትም ከመጀመሪያው በላቀ ከፍተኛ መጠን ላለው ቫይረስ ተጋልጦ ሊሆን ይችላል።

ለመጀመሪያው ቫይረስ የዳበረው በሽታ የመከላከል አቅም ሁለተኛውን ዙር ከባድ አድርጎት እንደሆነም ይገመታል።

የኢስት አንጅሊያው ፕ/ር ፖል ሀንተር “በሁለቱ ህመም መካከል ያለው ጊዜ አጭር መሆኑና ሁለተኛው ዙር ከመጀመሪያው መባሱ አሳሳቢ ነው” ይላሉ።

የአሜሪካውን ግልሰብ የተመለከተው ጥናት ምን ይጠቁማል? ለሚለው ምላሽ ለመስጠት ገና ነው ብለዋል ፕ/ር ፖል።