ኮሮናቫይረስ ፡ የያዘዎት ጉንፋን ወይስ ኮቪድ-19 መሆኑን እንዴት መለየት ይችላሉ?

ምታስነጥስ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢንፍሉዌንዛ፣ ጉንፋን እና ኮቪድ-19 መነሻቸው የተለያዩ ቫይረሶች ቢሆኑም፤ ምልክታቸው ተመሳሳይ ነው። አንዳቸውን ከሌላቸው ለመለየትም ያስቸግራል።

በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ከሚያሳዩት ምልክት መካከል ሙቀት መጨመር፣ የማያቋርጥ ሳል፣ የስሜት ህዋሳት አልሠራ ማለት ይጠቀሳሉ።

ትኩሳት አለዎት?

ሙቀት ከ37.8 በላይ ሲጨምር ሰውነት ኮሮናቫይረስን ወይም ሌላ ህመም እየተዋጋ ነው ማለት ነው።

ስለዚህም ቴርሞሜትር ካለዎት ሙቀትዎን ይለኩ። ከሌለዎ ደግሞ ደረትዎ ወይም ጀርባዎ ላይ ትኩሳት እንዳለዎ በአይበሉባዎ ይፈትሹ።

ትኩሳት የኮሮናቫይረስ ብቻ ሳይሆን የጉንፋንና የሌሎች ህመሞችም ምልክት ነው። ትኩሳት ካለዎት ኮቪድ-19 ቢመረመሩ ይመከራል።

ያስልዎታል?

ኢንፍሉዌንዛ ወይም ጉንፋን ሲይዝዎ ያስልዎታል።

ጉንፋን ድንገት ይከሰትና የጡንቻ ህመም፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ራስ ምታት፣ የጉሮሮ መድረቅ፣ ድካም፣ የአፍንጫ መታፈን ያስከትላል። ህመሙ ከኢንፍሉዌንዛ በላይ ነው።

ኢንፍሉዌንዛ የሚሰማን ቀስ በቀስ ሲሆን፤ ህመሙም ቀለል ይላል። ሳል፣ ማስነጠስ፣ የጉሮሮ መድረቅ እና የአፍንጫ ፈሳሽ ምልክቶቹ ናቸው። ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ የጡንቻ ህመምና ራስ ምታት ላይገጥምዎ ይችላል።

ኮሮናቫይረስ ሲይዝዎ ከአንድ ሰዓት በላይ ያስላሉ። በ24 ሰዓት ውስጥ ሁለቴ ወይም ሦስቴ የማያቋርጥ ሳልም ያስከትላል።

የማያቋርጥ ሳል ከገጠመዎ ኮቪድ-19 እንዲመረመሩ ይመከራል።

Woman coughing

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መቅመስና ማሽተት አለመቻል

ማሽተት ካቃተዎ ወይም ጣዕም መለየት ካልቻሉ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረግ አለብዎት።

ቀለል ያለ ብርድ ይዞዎት ሊሆን ቢችልም መመርመሩ አይከፋም።

በሌላ በኩል ማስነጠስ የኮሮናቫይረስ ምልክት አይደለም። ትኩሳትና ሳል ከሌለዎ ወይም የስሜት ህዋስዎ እንደ ወትሮው እየሠሩ ከሆነ መመርመር አያስፈልግዎትም።

ሆኖም ግን ሲያስነጥሱ ቫይረሱን ሊያስተላልፉ ስለሚችሉ ሶፍት ይጠቀሙና እጅዎን በሳሙና ይታጠቡ።

እጅ ከመታጠብ በተጨማሪ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግና አካላዊ ርቀት መጠበቅም አይዘንጉ።

አፍንጫዎን ያፍንዎታል?

የአፍንጫ ፈሳሽ የኮሮናቫይረስ ምልክት እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ኮቪድ-19 ያለባቸው ሰዎች መጠነኛ ወይም የተባባሰ ምልክት ሊያሳዩ ይችላሉ። ምልክት የማያሳዩ ሰዎች በሽታውን ሊያስተላልፉ ይችላሉ።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በሁለት ሳምንት ውስጥ ምልክቱን ያሳያሉ። በእርግጥ ብዙሀኑ በአምስተኛው ቀን የበሽታው ምልክት ሊታይባቸው ይችላል።

ትንፋሽ የሚያጥርዎ ከሆነ በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ነው።

በአጠቃላይ አንዳች የኮቪድ-19 ምልክት ሰውነትዎ ላይ ካስተዋሉ ሳያንገራግሩ ወደ ህክምና መስጫ ይሂዱ።

ምልክቶች
ኮሮና
Banner